በቋራ ወረዳ ከ200 በላይ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ቃጠሎ መውደማቸው ተገለጸ

108

ሚያዝያ 18/2011  በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ነፍስ ገበያ ቁጥር አራት ተብሎ በሚጠራው የገጠር ከተማ ከ200 በላይ መኖሪያ ቤቶች  በእሳት ቃጠሎ መውደማቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ አዲሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከትናንት በስቲያ ምሽት ስድስት ሰዓት አካባቢ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከ200 በላይ አባወራዎች ያለመጠለያ ቀርተዋል፡፡

ሰው ከማይኖርበት ከአንድ የሳር ጎጆ ቤት የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በአካባቢው በሚገኘው የመከላከለያ ሰራዊት አባላትና በከተማው ነዋሪዎች ርብርብ ከስድስት ሰዓታት ጥረት በኋላ  መቆጣጠር ተችሏል፡፡

"በአካባቢው የነበረው ኃይለኛ ንፋስ ለእሳት ቃጠሎ መባባስና በፍጥነት መስፋፋት ምክንያት ሆኖኗል" ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፡፡

የቤቶቹ ተጠጋግቶ መሰራትም እሳቱን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎት እንደነበርም አስረድተዋል።

በእሳት ቃጠሎው ከወደሙ ቤቶችና ንብረት በስተቀር በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩንም አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡

በቃጠሎው ቤት ንብረታቸው በመውደሙ መጠለያ አልባ የሆኑ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም  የሚያስፈልገው ለመለየት   አንድ አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም