በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ ከ315 በላይ የቤት እንስሳት በአናብስት ተበሉ

108

ጋምቤላ ሚያዝያ 18 / 2011 በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ  ከ315 በላይ የቤት እንስሳት በአናብስት እንደተበሉባቸው ነዋሪዎቹ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አናብስቱ እያደረሱት ያለውን ችግር በተጠና መልኩ ለመፍታት እየተንቀሳቀስኩ ነው ይላል።

በወረዳው የመንደር 11ና 12 ቀበሌ  ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አናብስቱ በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት ያደረሱት በዚህ ዓመት በተለያየ ጊዜ ነው።

አናብስቱ እያደረሱ ባለው ጉዳት በዚህ ወር ብቻ 14 የቤት እንስሳት እንደተበሉባቸውም አመልክተዋል።

ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አዲሱ ቡርቃ አናብስቱ  እያደረሱ ባለው ጉዳት በተለያዩ ጊዜያት አምስት የዳልጋ ከብትና አንድ ፍየል እንደተበላቸው ይናገራሉ።

አደጋው እየተደጋገመ ከመምጣቱ አንጻር በሰው ላይም ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።

አናብስቱ በከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምሽት ላይ ወደ ሰፈር ዘልቀው በመግባት እንስሳቱን ከበረት አስደንብረው በማስወጣት ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ አባተ ናቸው።

አናብስቱ እያደረሱት ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እሳት በማንደድና ባትሪ በማብራት ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያወሱት አስተያየት ሰጪ፣ ችግሩ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው መኖሪያዬን ለመልቀቅ እያሰብኩ ነው ብለዋል።

የመንደር 12 ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ጃንጎሎ እንዳሉት አናብስቱ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተበሉትን ጨምሮ 315 የዳልጋ፣ የጋማ ከብቶችና ፍየሎችን በተሰማሩበትና ከበረት በማስደንበር መብላታቸውን ተናግረዋል።

በወደ መኖሪያ ሰፈሮች ዘልቀው በመግባት በሰው ላይ ጉዳት ያደርሱብናል የሚል ስጋት በነዋሪዎች ላይ እንደሚታይ ገልጸዋል።

በኢትየጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሄኖክ ታምሩ ስለጉዳዩ ተጠይቀው  አናብስቱ  እያደረሱት ያለው ጉዳት ለመከላከል በባለሙያዎች ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

አናብስቱ  ከኣካባቢው ለማስወገድ  ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀምና ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር ችግሩን ለማስወገድ መታሰቡን አስታውቀዋል።

በአናብስቱ ጉዳት ባደረሱባቸው ቀበሌዎች ባደረጉት ምልከታም በርካታ የተበሉ የቤት እንስሳት ቅሪት መገኘቱን አስረድተዋል።

በአካባቢው አምስት አንበሶች  ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

አናብስቱ ጉዳቱን የሚያደርሱት የአካባቢው ደን በመጨፍጨፉና የሚመገቧቸው የዱር እንስሳት ከአካባቢው በመጥፋታቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

በአናብስቱ ጉዳት እያደረሱባቸው ያሉት ቀበሌዎች ከፓርኩ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑንም ተወካዩ አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በበተካሄደ ጥናት በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክና በአካባቢው ከ500 በላይ አናብስት እንደሚገኙ ከፓርኩ ጽህፈት ቤተ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም