የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ስርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል

121
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በድንገተኛ ህመም ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ስርዓተ ቀብር በነገው ዕለት በማይጨው ከተማ  ይፈጸማል፡፡ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ለኢዜአ እንደገለጹት በአሜን ሆስፒታል የሚደረገው የአስከሬን ምርመራ እንደተጠናቀቀ አስከሬኑ ወደ ማይጨው ይሸኛል፡፡ በነገው እለት ደግሞ ስርዓተ ቀብራቸው በማይጨው ከተማ እንደሚፈጸም ነው የገለጹት፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ወደ እግር ኳስ ህይወት ከመግባታቸው በፊት  በውትድርና አገልግለዋል። በ16ኛ ክፍለ ጦርና በምድር ጦር ውስጥም በእግር ኳስ ተጫዋችነት አሳልፈዋል። በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን ጀምረዋል። አሰልጣኝ ንጉሴ መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት እና ወልዲያ እግር ኳስ ክለቦችን በአሰልጣኝነት የመሩ ሲሆን ከ2010 ጀምሮ  ደግሞ በድጋሚ ወደ ደደቢት ተመልሰው ነበር። አሰልጣኙ በ2005 ዓ.ም ከደደቢት ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወሳል። በ2008 ዓ ም ወልድያ ከተማን  ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመጣ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። የአሰልጣኙን ህልፈተ ህይወት ተከትሎም ደደቢት ዛሬ ከአርባምንጭ ጋር የሚያደርገው የ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወደፊት በሚወጣ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል። ፌደሬሽኑ  በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሀዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለደደቢት እግር ኳስ ክለብና ለእግር ኳስ ቤተሰቦች በሙሉ መፅናናትን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም