ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመሩ

81

ሚያዝያ 17/20011 በአሮሚያ ምዕራብ ጉጂ እና በደቡብ ጌዴኦ አጎራባች አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጎች  ዛሬ ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመሩ።

ለተፈናቃዮቹ  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት አስታውቀዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ወደ ቄያቸው መመለስ የጀመሩት የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በተገኙበት የእርቅ ስነስርዓት ከተካሄደ በኋላ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች መካከል ምንም አይነት ግጭት የለም፡፡

ሁለቱም ህዝቦች የቀድሞ አንድነታቸውና አብሮነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ  መንግስትም ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  አቶ ሽመልስ አረጋግጠዋል፡፡

ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው በመመለስ የቀደመ ኑሮቸውን ተረጋግተው እንዲቀጥሉም ድጋፋቸው እንደማይለያቸው  ገልጸዋል፡፡

ከሰብአዊ ድጋፍና ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ስጋትም ቀድሞ የነበረው ችግር ዳግም እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

"በተለይም በማፈናቀል  ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ በመውሰድ የደህንነት ስጋትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀነስ በመስራት ላይ ነን "ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች እርስ በእርስ የሚተዋወቁና የሚተማመኑ በመሆኑ ችግሩን የሚያባብሱ አካላትን አጋልጦ በማውጣት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በበኩላቸው የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ ክልል መንግስታት በትኩረትና በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጉጂና የጌዴኦ ህዝቦች የቆየ አንድነታቸውን ጠብቀው  መቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በኦሮሚያም በደቡብ መኖራቸውን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  የፌደራል መንግስት የምግብ፣ የጤና መሰል ሰብዓዊ ድጋፎችን እያቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አባገዳዎች በምርቃት የእርቅ ስነ ስርዓት ያካሄዱ ሲሆን የወረዳው ህብረተሰብም ተፈናቃዮችን ለመቀበል ከስምምነት ተደርሶ ነው ወደ ቀያቸው የመመለሱ እንቅስቃሴ የተጀመረው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም