በጥምረት ለመስራት የተደረገ ስምምነት ተፈረመ

82

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011  የምግብ መጠጥና ፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በጥምረት መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ በግብርና ምርት ላይ እሴት በመጨመር የጥጥ ንግዱን በማሻሻል ገቢ ለማግኘት እንዲሁም ለምግብና መጠጥ ዘርፍ ጥራትን ለማሻሻል ያለመ ነው።

የምግብ መጠጥና ፋርማሲውቲካል ኢንደስትሪ ልማት ዘርፉን አቅም ማጎልበት፣ ጥናት ምርምር ማካሄድ እንዲሁም የማማከርና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ስምምነቱ የሚያተኩርባቸው ናቸው።

በዘርፉ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሀይል፣ በጥናትና ምርምር የዳበሩ ስራዎችን የሚያበረክቱ ላቦራቶሪዎች እና አዳዲስ የጥናት ውጤቶች ከስምምነቱ የሚጠበቁ ናቸው።

የአገሮች የምጡቅነት ደረጃ የሚለካው "የምግብ ስታንዳርዱ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ተመዝኖ ነው" ያሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ፤ ስምምነቱ በአገሪቷ ያሉ በምግብና መጠጥ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎችን በፈቃደኝነት ላይ ከተመሠረተ የምግብ ስታንዳርድ የማስጠበቅ ስራ ወደ አስገዳጅነት እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል።

ስለሆነም ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ለተሠማሩ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ባቀረበባቸው የማወዳደሪያ መስፈርቶች መሰረት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተሻለ ሳይንሳዊና ተግባር ተኮር በመሆኑ መመረጡን አስታውሰዋል።

የበለስ የምግብ ላቦራቶሪ አገልግሎት ዳይሬክተርና ሊቀ መንበር አቶ በለጠ በየነ እንደገለጹት  ስምምነቱ የአገራችን የልህቀት ተቋማት በተለይ ዩኒቨርሲቲዎቹ ችግር ፈች ሥራዎችን ለመስራት ወደ ህብረተሰቡ መቅረባቸውን፣ ኢንስቲትዩቱ ደግሞ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከአገር በቀል የልህቀት ማዕከላት ጋር ጥምረት መፍጠሩ ለሌሎችም የሚበረታታ መሆኑን ያሳያል።

አያይዘውም የአገራችን የምግብ መጠጥ ኢንዱስትሪዎች በጥራት፣ በይዘት፣ በመጠን ከፍ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸው በአገርም ሆነ በውጭ ከፍ እንዲል በር ይከፍታል።

ስምምነቱ ተቋሙ በ2017 ዓ.ም ሊያሳካው ያስቀመጠውን የምግብ መጠጥና አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ራእይ ለመድረስ ይጠቅመዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት አገሪቷ 1ሺ 242 በምግብና መጠጥ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎች እንዳሏት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም