ፖሊስ የስቅለትና የፋሲካ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

72

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የስቅለትና የፋሲካ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራው ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሚያዚያ 18 እና 20 2011 ዓ/ም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩት የስቅለትና የትንሳኤ በዓላት በሰላም እንድከናወኑ ዝግጅቱን አጠናቋል።

 ኮሚሽኑ ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ አባላትን በስውርና በግልፅ ጥበቃ በልዩ ልዩ ስፍራዎች ማሰማራቱን አስታውቋል።

የኮሚሽኑን የኢንዶክተሪኔሽን እና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካን የጠቀሰው መግለጫው ከሌሎች የፀጥታ አካለት ጋር በመቀናጀት በመዲናዋ አስሩም ክፍለ ከተሞች በፀጥታ ጉዳይ ቀደም ብሎ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉ ተመልክቷል።

በዓሉ ሲከበር ህዝቡ ከሌሎች የፀጥታ አካለት ጋር ተቀናጅቶ እየሰተራ መሆኑን በመገንዘብ ለፀጥታ ስራው ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር እንዲያጠናክርም ተጠይቋል።

ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት 991 ወይም 987 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11 ፣ 01- 15- 52 - 63- 03 መጠቀም እንደሚቻል ተገልጿል።

ኮሚሽኑ ለስራው ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ትብብር በማመስገን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም