የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ምቹ አጋጣሚ ሙያን መሰረት አድርገው እንዲጠቀሙ በስልጠና መታገዝ አለባቸው-ባለሙያዎች

379

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 መገናኛ ብዙሃን በተፈጠረላቸው ምቹ አጋጣሚ ሙያን መሰረት አድርገው እንዲጠቀሙ በስልጠና መታገዝ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃን በተፈጠረላቸው ምቹ አጋጣሚ ሙያን መሰረት አድርገው እንዲጠቀሙ በስልጠና መታገዝ እንዳለባቸው  ተገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመስኩ ባለሙያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከመቸውም በበለጠ ምቹ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋ ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ጋዜጠኞች ሙያቸውን መሰረት አድርገው እንዲሰሩ ከማድረግ አንጻር ምቹ አካባቢ ባለመኖሩ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተጽእኖ ነጻ ሆነው እንደፈለጉ የመዘገብ ሁኔታ ቢስተዋልም የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ሙያው ከሚፈቅደው በታች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል።

መገናኛ ብዙሃን የጋዜጠኝነትን ሙያ መሰረት አድርገው ብቻ ስራቸውን እንዲያከናውኑ መንግስት ከተጽእኖ ነጻ አድርጓቸዋል ሲሉ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር በማነጻጸር ተናግረው የተሰጣቸውን እድል ግን እየተጠቀሙበት አይደለም ይላሉ።

ቀደም ሲል ይሰሩበት ከነበረው ተጽእኖ ለመውጣትና የስራ አካባቢውን ምቹ አድርጎ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሶስት ነጥቦች ላይ ማለትም ስልጠና መስጠት በነጻነት እንዲሰሩ ማበረታትና በመንግስት በከኩል  መረጃ ክፍት ማድረግ ላይ መሰራት እንደሚገባ  ባለሙያው ይመክራሉ። 

የካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ግሩም አባተ በበኩላቸው ከነጻነት ጀምሮ በኢትዮጵያ አሁንም ለጋዜጠኝነት ሙያ ሙሉ ለሙሉ ለስራ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም የሚል አቋም እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአዲሰ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ የአዲስ ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ሃላፊ ጋዜጠኛ ሙባረክ መሃመድ ደግሞ የጸረ ሽብር ህጉን ጨምሮ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አሳሪ የነበሩ ህጎች እየተሻሻሉ መሆኑን እንደ በጎ ጅምር ያነሳሉ።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ዝግ የነበሩ ተቋማት ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት ቢሆኑም በተለይም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች የሚሉትን ከማስተጋባት በዘለለ ታች ድረስ ወርደን እየሰራን አይደለም በማለት በቀጣይ ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተዛመዱ ስልጠናዎችና መሰረተ ልማቱ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር እየተሰራባቸው ካሉ ዘርፎች አንዱ ሚዲያው እንደሆነ ይታወቃል።