በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማራን ባለሀብቶች በቂ ድጋፍ እያገኘን አይደለም አሉ

119
ሚያዝያ17/2011 በአዲስ አበባ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ ያወጡ የከተማዋ ባለሃብቶች በቂ ድጋፍ እንደማያገኙ ገለጹ። የከተማው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ "ከእኔ የሚፈልጉትን ነገር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እያቀረብኩ ነው" ብሏል። ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከተሰማሩ የከተማዋ ባለሃብቶች ጋር ባጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል። በውይይቱ ላይ ሐሳባቸውን ያቀረቡት ባለሀብቶች እዳሉት ለተሰማራንባቸው የልማት ዘርፎች የሚመጥን ድጋፍ እየተሰጠን አይደለንም ብለዋል። የዋሴ ፋርማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ ዳዊት ዋሲሁን እንዳሉት፤ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ አያገኝም። አቶ ዳዊት አክለውም ከኮሚሽኑ የሚሰጠን ድጋፍና ትብብር ፈጣን ቢሆንም ከሌሎች ጋር በቅንጅት የሚሰሩ ጉዳዮችን በተመለከተ በወቅቱ ምላሽ ለማግኘት አዳጋች ነው ይላሉ። ከሶስት ዓመት በፊት የመሬት ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የገለጹት አቶ ዳዊት፤ "በዚህ የተንዛዛ አሰራር ለከተማዋ ጠብ የሚል ነገር መስራት አንችልም" ብለዋል። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የአሹ ኢንተርናሽናል ፈርኒቸር ባለቤት አቶ አሸናፊ ሙሴ በኮዬ ፈጬ አካባቢ ከ200 በላይ መካከለኛ ባለሃብቶ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደን መሬት በሊዝ ገዝተን ወደ ስራ ለመግባት አልቻልንም ብለዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች የልማት ተነሺዎች ተብለው ተገቢውን የሊዝ ክፍያ ከከፈልን በኋላ ወደ ስራ የምንገባበትን ማመቻቸት የሚገባው መንግስት ነው ያሉት አቶ አሸናፊ የልማት ተነሺዎች ተብለው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ በተፈናቃይ ስም ሌላ መጓተት መፈጠር የለበትም ብለዋል። መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን የሚንከባከበውን ያህል የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን እየተንከባከበ አይደለምም ብለዋል ባለሃብቶቹ። በመሆኑም ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል ነው ያሉት። የአዲስ አበባከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ በበኩላቸው ባለሃብቶች ለሀገሪቷ እድገት ወሳኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም አዲስ አበባን በአፍሪካ ቀዳሚ፣ ምቹና ተመራጭ የኢንቨስትመንት ከተማ ለማድረግም ከአገር ወስጥ ባለሃበቶች ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል። የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ለገቢ ንግድ የሚወጣውን ምንዛሬ በማስቀረት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአገር ያላቸው ፋይዳ የላቀ በመሆኑም ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል። ባለሃብቶችም ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጎማ ፈቃድ ላወጡበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል። ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለከተማ አስተዳደሩ ሆኖ በጠንካራ አደረጃጀት መዋቀሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን አቅም ለማጎልበትና ለማበረታታትም አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም