ትንሳዔን በዜጐች መካከል ፍቅርና መከባበር እንዲጐለብት በማስተማር እናከብረዋልለን-- የፍቼና የነጌሌ ከተሞች ነዋሪዎች

70
ፍቼ ሚያዝያ 17/2011የትንሳኤ በዓል በአገሪቱ የተገኘው ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠልና በዜጐች መካከል ፍቅርና መከባበር እንዲጐለብት በማስተማር እንደሚያከብሩት በኦሮሚያ ክልል የፍቼ የነጌሌ ከተሞች ነዋሪዎች አመለከቱ። የትንሳኤ በዓል በአገሪቱ የተገኘው ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠልና በዜጐች መካከል ፍቅርና መከባበር እንዲጐለብት በማስተማር እንደሚያከብሩት በኦሮሚያ ክልል የፍቼ የነጌሌ ከተሞች ነዋሪዎች አመለከቱ። ትንሳዔ  የምህረት የመቻቻልና የመረዳዳት ሃይማኖታዊ በአል በመሆኑ ቂምና ጥላቻን በመተው እንደሚያከብሩትም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ሺፈራው ተሰማ  ሃይማኖታዊ ፣ባህላዊና ታሪካዊ የማንነት ሃብቶችን  በመጠበቅና በመንከባከብ ለአገራችን ሰላም የምንሰራበት የምንተሳሰብበት በዓል  ሊሆን ይገባል ብለዋል። ልማትን በማጠናከር፣ በመቻቻል ለሰላም ፣ለወንድማማችነትና ለእድገት በጋራ መስራትና ማስተማር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ። የበዓሉም ዓላማ  በሰዎች መካከል ፍቅር ፣ሰላምና ትህትና ለማስተማር  ክርስቶስ የከፈለውን አርዓያነት በግለሰብ ደረጃ እንድናሳይ ምሳሌ መሆን ነው ብለዋል ። የከተማው ነዋሪ  መጋቢ በኩረ ህይወት ፈረደ  በዓሉን የሚያከብሩት የአገር ታሪክና የማንነት መገለጫ የሆኑ የሰላም፣ የፍቅር ትውፊቶችን በማጐልበትና ለሌሎች በማስተማር እንደሆነ ገልጸዋል። በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አሰግድ ጎሹ በበኩላቸው በዓሉን አቅመ ደካማ ወገኖችን በምግብና በአልባሳትከመደገፍ ባሻገር፤ ለአገር ሰላምና ወዳጅነት በመፀለይ እንደሚያከብሩት ተናግረዋል። የፍቼ ከተማ ከንቲባ አቶ ሁንዴ ከበደ  በበኩላቸው በዓሉን ከተማቸውን የማፅዳትና  የማስዋብ ስራ ጨምሮ ሆቴሎች እንግዶችን እንዲያስተናግዱ፣ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይፈፀም የሚመለከታቸውን ወገኖች በማነፅና በማስተማር እንደሚያሳልፉ አመልክተዋል ። የነጌሌ ከተማ ነዋሪው ቀሲስ መለሰ ነጋ ከተማዋ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዎች በመቻቻልበመከባበርና በመረዳዳት በጋራ የሚኖሩበት የፍቅር ከተማ  እንደመሆኑ፤ በሰላም በፍቅርና በአብሮነት አንደሚያከብሩት ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ሃይማኖት የግል ቢሆንም ክርስቲያኑ የእስላሙን፣ እስላሙ ደግሞ የክርስቲያኑን በዓል በማክበር በመጠራራት አብሮ በመብላትና በመጫዋት እንደሚያሳልፉት  ተናግረዋል፡፡ በዓሉን ከቂምና ከጥላቻ በመራቅ የፈጣሪያችንን መልካም አርአያና ስራ በማሰብና በመከተል ማክበር እንደሚገባም መክረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ሼክህከድር አብዱረህማን ወጣቱ ቂም ጥላቻና በቀልን በመተው በአብሮነት በዓሉን በጋራ በማክበር የአባቶቹን መልካም ባህል ማስቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት አበራ ሞገስ የአባቶቻችን የመቻቻል የመረዳዳትና የአብሮነት ባህላዊ እሴት ለማስቀጠል በበዓሉ የተቸገሩን መርዳት ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ልናደርገው ይገባል  ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም