የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀቁ

67
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀዋል። ሚኒስትሩ ከኖርዌይ አቻቸው ኤሪክሰን ሶርይዴ ጋር ትናንት በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ከኖርዌይ የፓርላማ የውጭ ጉዳዮችና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አኒኬን ሁት ፊልደት ጋርም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል። የፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በዶክተር ወርቅነህ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። የኖርዌይ የፓርላማ ውጭ ጉዳዮችና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያና በሌላ አንድ ተጨማሪ የአፍሪካ አገር የስራ ጉብኝት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል። የኖርዌይ የማዳበሪያ አምራች የሆነው ያራ ኢንተርናሽናል ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ከዶክተር ወርቅነህ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮዮጵያ በግብርናው መስክ ለመሰማራት እንደሚፈልግ መግለጹን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም