ሚኒስቴሩ ለሦስት ኩባንያዎች የማዕድን ምርመራ ፍቃድ ሰጠ

101
ሚያዝያ 16/2011 የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ፍለጋ ለማካሄድ ፍቃድ ጠይቀው መስፈርቱን ላሟሉ ሦስት ኩባንያዎች የምርመራ ፍቃድ ሰጠ። ሚኒስቴሩ ፍለጋውን እንዲያካሄዱ ስምምነት የተፈራረማቸው ኩባንያዎች መካከል አይጋ ትሬዲንግ ኢንዱስትሪስ፣ ሂምራ ማይኒንግና የቻይናው ዶንግ ፊ ናቸው። በስምምነቱ መሰረትም ኩባንያዎቹ በትግራይ፣አማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ ማዕድናትን ምርመራ ያደርጋሉ፤ በወርቅ፣ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት እንዲሁም በከሰል ድንጋይ ማዕድናት ፍለጋ ላይ ይሰማራሉም ነው የተባለው። ለፍለጋው ወጪ በአጠቃላይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት የሚያደርጉት ኩባንያዎቹ ለ46 የፍለጋ ባለሙያዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ነው የተገለጸው። ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት 56 ኩባንያዎች ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፍተሻ እየተደረገ መስፈቱን  ላሟሉት ፍቃድ እየተሰጠ ነው። ከሳምንት በፊት ለ8 ኩባንያዎች ተማሳሳይ የምርመራ ፍቃድ እንደተሰጠ በማስታወስ። ለኩባንያዎቹ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተግባራት እንደተጀመረ የጠቀሱት ሚኒስትሩ በተለይም የሚያለሙበት ክልሎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበት ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል። ''ዛሬ ስምምነት የፈረማችሁ ኩባንያዎች ውጤታማ እንድትሆኑ መንግሥት የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ" ሲሉም  ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኩባንያዎቹ ውሉን መሰረት አድርገው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም