የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደር እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ የሚያሰራ መሆን አለበት--የተወካዮች ም/ቤት

111
ሚያዝያ16/2011 የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደር እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ ሊያሰራና ተፈፃሚነቱ የማያሻማ እንዲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። በአገሪቷ እየተፈጠረ ያለው የማዕድን ገበያ ከዚህ በፊት የነበረውን የከበረ ማዕድን ግብይት አዋጁን ወደ ማዕድን ግብይት ለመቀየር ምክንያት ሆኗል ተብሏል። የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደር እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ የሚያሰራና ተፈፃሚነቱ የማያሻማ ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል። ቋሚ ኮሚቴው በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እየተዘጋጀ ባለው የማዕድናት ግብይት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በዛሬው እለት አካሂዷል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ ዩሲፍ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ምክር ቤቱ በ2001 አዋጅ ቁጥር 651/2001 የከበሩ ማዕድን አዋጅን አውጥቶ እስካሁን እየተሰራበት ይገኛል። ይሁንና አዋጁ ውስን የሆኑ የከበሩ ማዕድናት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ያለውን የማዕድናት መጠንና ብዛትን ያማከለ አይደለም። በመሆኑም እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የማዕድን ግብይት ለማስተዳደር እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ የሚያሰራና ተፈፃሚነቱ የማያሻማ መሆን አለበት ብለዋል። ግልጸኝነትን ያሰፈነ፣ የማያሻማ ቃላት ያሉት፣ ሃገራዊ ቋንቋን የሚጠቀም፣ከሌላ ተቋማት ጋር የሚተያዩ አዋጆችን በግልጽ የሚጠቅስና የትርጉም ይዘቱ የማያሻማ መሆን እንደሚገባም አብራርተዋል። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየተፈጠረ ያለው የማዕድን ገበያ መስፋት ከዚህ በፊት የነበረውን የከበረ ማዕድን ግብይት አዋጁን ወደ የማዕድን ግብይት ለመቀየር ምክንያት ሆኗል። በዚህም በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ገበያ ላይ በርካታ አዳዲስ ማዕድናት መኖራቸው፣ ክልሎች ለማዕድን ግብይት ለነጋዴዎች ፍቃድ  እንዲሰጡ ለማስቻልና ህገ ወጥ ወይም ኮንትሮባንድ የማዕድን ግብይት ለማስቀረት አዋጁን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል። በመሆኑም በአዋጅ 651/2001 መሰረት ውስን የነበረው የማዕድን ግብይት በማስቀረት የከበሩ ማዕድናት፣ በከፊል የከበሩ ማዕድናት፣ብረት ነክ ማዕድናት፣የኮንስትራክሽን ማዕድናትና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በአዲሱ አዋጅ እንዲካተቱ ተደርጓል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም