በመስኖ የሚለሙ ምርቶች ተጨማሪ ገቢ እንደፈጠሩላቸው በመቀሌ ከተማ በአነስተኛ የጉልት ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ገለጹ።

67
ሚያዝያ 16/2011 በመስኖ የሚለሙ ምርቶች ኑሮአቸውን የሚያሻሽል ገቢ እንደፈጠሩላቸው በመቀሌ ከተማ በአነስተኛ የጉልት ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ተናገሩ። በትግራይ ክልል በመስኖ የሚለማው መሬት ስፋት ወደ 48ሺህ ሄክታር  ማደጉን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታውቋል። ከሴቶቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በከተማዋ እያደገ ከመጣው የመስኖ ልማት ምርት ሕይወታቸውን የሚለውጥ ገቢ እያስገኙላቸው ነው። በመቀሌ ከተማ በሐውልት ክፍለ ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬሽያጭ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ መረስዒት ፀጋይ እንደገለጹት ከአምራች አርሶ አደሮች በየቀኑ 25 ኪሎ ግራም ቆስጣ በ250 ብር ሂሳብ እየገዙ በችርቻሮ ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ። ልማቱ እሳቸውን ጨምሮ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩት የከተማው ነዋሪዎች እየጠቀመና ሥራ  እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የጓሮ አትክልቱን በችርቻሮ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የገዙበትን ወጪ ሸፍነው በየቀኑ እስከ 150 ብር ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ከሽያጩ ከሚያገኙት ገቢ ለተከራዩት አነስተኛ ቤት በየወሩ 500 ብር ከመክፈል ባለፈ አምስት ልጆቻቸውን ወጪያቸውን ሸፍነው እያስተማሩ መሆኑን አስረድተዋል። የበተመሳሳይ ስራ የተሰማሩት ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ህሉፍቲ አብርሃ በበኩላቸው ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ ልዩ ስሙ ሰሰላ እየተባለ ከሚጠራው ገጠር ቀበሌ በየቀኑ ወደ መቀሌ ከተማ ከሚገባው ቃሪያ 100 ኪሎግራም በ2 ሺህ ብር በመግዛት ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል። በምግብ ዝግጅት ለተሰማሩና በግል ለሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች አንድ ኪሎ ቃሪያ በ30 ብር ሂሳብ በመሸጥ ወጪያቸውን ሸፍነው ከአንድ ሺህ ብር በላይ የተጣራ ትርፍ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። በገቢውም ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በሓድነት ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ወይዘሮ ብርሃን ሰሎሞን በበኩላቸው የአትክልት ምርቶች ከትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች እየተቀበሉ ለከተማው ኅብረተሰብ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። "የንግድ ስራው አድካሚ ቢሆንም በየቀኑ እስከ 200 ብር ትርፍ እያገኘሁ ኑሮዬን በሚገባ እየመራሁ ነው" ብለዋል። የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ እንደገለጹት በትግራይ ክልል በመስኖ ከሚለሙ ምርቶች የከተማዋን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርገዋል። በዘርፉ የተሰማሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በ4 ሺህ ሄክታር ብቻ የተወሰነው የመስኖ ልማት አሁን ወደ 48 ሺህ ሄክታር ማደጉን ተናገግረዋል። በመስኖ ልማት ስራው ከ200 ሺህ የሚበልጡ የክልሉ አርሶ አደሮች፤ ወጣቶችና ሴቶች ተጨማሪ የገቢ ምንጭና ሥራ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል። በዚህ ዓመት በአንድ ዙር ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለከተማው ነዋሪዎች መቅረቡን አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም