የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የናይሮቢ ቅርንጫፍ ዘላቂነት እንዲኖረው ጠንካራ የመረጃ ስርዓት ይፈጠራል-ኤምባሲው

47
ሚያዝያ 16/2011 በተሟሟቀ መልኩ የተጀመረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የኬንያ ናይሮቢ ቅርንጫፍ ዘላቂነት እንዲኖረው ጠንካራ የመረጃ ስርዓት እንደሚፈጠር በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ። በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደ ስነስርዓት በይፋ የጀመረው የናይሮቢ ምዕራፍ በርካቶች በንቃት የተሳተፉበት እንደነበር ይታወሳል። በዕለቱም በመድረኩ የተሳተፉ በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመሳተፍ ለአገራቸው አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት እንዳላቸውም አሳይተዋል። የሚጠበቅባቸውን መዋጮም ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ አድርገዋል። ኢዜአ በቦታው ተገኝቶ ያነጋገራቸውናበኬንያ ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩት አቶ መሐመድ ሼቡ እንዲሁም ለአምስት አመታት ኑሮውን በኬንያ ያደረገው ወጣት ደለለኝ ታደሰ ለኢትዮጵያ ልማት በሚውለው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ዘላቂ እንደሚሆን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አገራዊ ኮሚቴ አባልና የናይሮቢ ምዕራፍ አስተባባሪ ገብርኤል ንጋቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትረስት ፈንድ ድጋፉ ዘላቂነት እንዲኖረው የእርስ በርስ ትስስርን ማጠናከር ይገባል። በኬንያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ መካከልም አንድነት፣ ፍቅርና ይቅር መባባል እንዲሰፍን በማድረግ ድጋፉን ቀጣይ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ማህበረሰቡ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቤቱ፣ የኢትዮጵያ መንግስትደግሞ መንግስቱ እንደሆነ እንዲያምን መደረግ እንዳለበትም ተናግረዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው የተጀመረው ‘አንድ ዶላር ከአንድ ማኪያቶ’ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ግልጽነት የተላበሰ የመረጃ ስርዓት መፈጠር እንዳለበት ነው የሚናገሩት። ለትረስት ፈንድ ገንዘብ የሚያወጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያዋጡት ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለ እንዲያውቁ ከተደረገ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ እምነቱን ገልጸዋል። የናይሮቢ ምዕራፍን እውን ለማድረግ ሲሰሩ የቆዩ የተለያዩ አካላትን ማጠናከርና የኮሚቴ ስብጥሩንም በማስፋት የማህበረሰቡን ተሳትፎ ዘላቂ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። ኤምባሲው የዳያስፖራው ድጋፍ እንዳይቀዛቀዝ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከነጋዴዎችና ከወጣቶች ጋርም በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል። የናይሮቢ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ዜጎች ራሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት የጀመሩት ሲሆን የኤምባሲው አስተዋጽኦ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ነበር። ኤምባሲው በራሱ አቅም ቀደም ብሎ ከፈጠራቸው አካላት ከተውጣጣ ኮሚቴ ጋር ተከታታይ ውይይት አድርጓል። በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በማድረግ አገራዊ ለውጡን በተመለከተ በቂ መረጃዎች ተደራሽ እያደረገም ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም