የአሜሪካው የግብርና ምርቶች ኩባንያ በኢትዮጵያ የሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ገለጸ

48
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2011 የአሜሪካው የግብርና ምርቶች ኩባንያ ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ በኢትዮጵያ የሰብሎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ። ኩባንያው አዲሱ ስያሜ የሆነውን 'ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ' የምርት መለያ (Brand Name) በኢትዮጵያ ይፋ የማድረግ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዷል። 'ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ' ከዚህ በፊት 'ፓዮኒር ሃይብሪድ' የሚል ስያሜ ነበረው። ከሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ራሱን በመቻል በግብርናው ዘርፍ እንደሚቀንሳቀስ የሚጠበቀው ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ፣ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች የሆኑት ዳው ኬሚካልና ዱፖንት ከሁለት ዓመት በፊት በፈጠሩት ውህደት አማካይነት እንደ አዲስ የተመሠረተ ኩባንያ ነው። ከዚህ ቀደም ፓዮኒር ሃይብሪድ ኢትዮጵያ በሚል ሥያሜ ላለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። የኮርቴቫ አግሪ ሳንይስ ኩባንያ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሬዚዳንት ሚስተር ፕራብዲፕ ባጅዋ በመድረኩ እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ለዚህም ከሰብሎች የሚገኘውን የምርት መጠን ማሳደግ እንደሚገባና ለዚህም ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ኩባንያው ድቅል ዘሮችንና ሰብሎችን የሚያጠቁ ተባዮችንና አረሞችን ለማጥፋት የሚያስችሉ ኬሚካሎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ከሰብሎች ከፍተኛ የምርት መጠን እንዲገኝ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አመልክተዋል። የሚቀርቡት ዘሮች የሚፈለገውን ምርት እንዲያስገኙ ኬሚካሎቹም በሰብሉና በከባቢው አየር ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ኩባንያው ከአርሶ አደሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮቹ ኬሚካሎቹንና ዘሮቹን የማስተዋወቅ ስራ እና አጠቃቀማቸው ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥና ዲጂታል የሆነ የዘርና ኬሚካል የግብይት ስርዓት እንደሚዘረጋም ነው ሚስተር ፕሪብዲዋ ያስረዱት። ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ ከአንድ ዓመት በፊት መናገሻ አካባቢ የዘር ማበጠሪያ ፋብሪካ ከፍቶ እየሰራ እንደሆነና ከአሜሪካ የሚያመጣቸውን ድቅል ዘሮች አበጥሮ ለአርሶ አደሮች ማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ላለፉት 26 ዓመታት ኩባንያው በኢትዮጵያ ለበቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች የሚሆኑትን ድቅል ዘሮችና ሰብል ከተባይና አረም የሚከላከሉ ኬሚካሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች በማቅረብ ምርታማነታቸውን እንዲያስድጉ አስችሏልም ብለዋል። ኩባንያው ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ፓላስ 45 የተሰኘውን ፀረ አረም የጤፍና የስንዴ ኬሚካል በማስተዋወቅ በምርታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳገኙና አርሶ አደሮቹም የመሰከሩለት እንደሆነ አውስተዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን ኩባንያው ባለው ቆይታ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል። ኩባንያው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የገበያ መዳረሻዎች አንዷ እንደሆነችና በግብርናው መስክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ትብብር አጠናክሮ እነደሚቀጥልም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር በበኩላቸው የኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ ኩባንያ በኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን ስራ ለማሳደግ ያሳየው ቁርጠኝነት የአሜሪካ የቢዝነስ ተቋማት በኢትዮጵያ የመስራት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላከት እንደሆነ ገልጸዋል። ኩባንያው የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የስራ እድል በመፍጠርና የግሉን ዘርፍ በግብርናው ያለው ተሳትፎ አንዲያድግና ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። በተጨማሪም ኩባንያው በኢትዮጵያ ስራውን ለማስፋት የጀመረው ስራ አሜሪካ በአሁኑ ሰአት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እያደረገች ላለችው ድጋፍ እንደ አጋዥ ተግባር የሚቆጠር እንደሆነም አመልክተዋል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ በግብርናው መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልና ለዚህም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሆነች ላረጋገጥ እወዳለሁም ብለዋል። የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የምርትና ምርታማነት መጨመር ዳይሬክተር ዶክተር ጭምዶ አንጫላ በኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙባቸው የሰብል ዘሮች ባህላዊና የሚፈለገውን ምርት የሚሰጡ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። ኮርቴቫ አግሪሳይንስ የሚያቀርባቸው ድቅል ዘሮች የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሰብሎችን የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግም ተናግረዋል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት መሰረት ያደረገው ግብርና ላይ እንደሆነና የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ጸረ-ተባይና አረም፣ ኬሚካሎችና ድቅል ዘሮችን በስፋት መጠቀም አስፈለጊ አንደሆነም አስረድተዋል። ኩባንያው በግብርና ምርምርና ጥናት ላይ የሚሰራ በመሆኑ ሳይንስና እውቀት ላይ መሰረት ያደረገ የግብርና እድገት በኢትዮጵያ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና የግብርና ምርት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያቀርብም አክለዋል። በአሜሪካ ኢንዲያና ግዛት ዋና መቀመጫውን ያደረገው ኮርቴቫ አግሪ ሳይስንስ በአሁኑ ሰዓት የገበያ ዋጋው 15 በሊዮን ዶላር ሲሆን በአጠቃላይ 20 ሺህ ሰራተኞች አሉት። ኩባንያው በ150 አገራት የሚሰራ ሲሆን በላቲን አሜሪካ፣በሰሜን አሜሪካ፣እስያ፣አውሮፓ፣አፍሪካና ኦሺኒያ አህጉራት ቅርንጫፎች አሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም