ከፍተኛ አመራሮች በጌዴኦ ዞን ካሉ ተፈናቃዮች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው

90
ሚያዚያ 16/2011 የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በጌዴኦ ዞን ካሉ ተፈናቃዮች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው። አመራሮቹ በጌዲኦ ዞን በሚገኙ አምስት መጠለያ ጣቢያዎች እየተካሄዱ ባለው ውይይት ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው ተመልሰው መኖር በሚችሉበት ዙሪያ   ይመክራሉ፡፡ ውይይቱን ተከትሎ ከነገ ጀምሮ ባሉት ቀናት ተፈናቃዮችን ደረጃ በደረጃ ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እንደሚከናወን ታውቋል። የጌዴኦ ዞን አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግስቱ ገዛኸኝ እንደገለፁት በመጀመሪያው ዙር ከቀርጫ ወረዳ በሚገኙ አስር  ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ  ይከናወናል። በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም  እስከ 15ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ወደ ቀይቸው እንደሚመለሱ  አመልክተዋል። ውይይቱን እየመሩ ካሉት አመራሮች መካከል በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ሽኩር እና በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ሙሳ ይገኙበታል። በውይይቱ የምዕራብ ጉጂና ጌዴኦ ዞን እንዲሁም የሁለቱ ክልል አመራሮች እየተሳተፉ  ሲሆን ከተፈናቃዮች ለሚነሱ  ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ መሆኑን  ሪፖርታራችን ከሰፍራው ዘግቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም