ግብፃውያን የፕሬዚዳንት አል ሲሲን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የተደረገውን ህገ መንግስታዊ ለውጥ በህዝበ ውሳኔ ደገፉ

52
ሚያዚያ 16/2011 የግብፅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በምርጫ ካሸነፉ በስልጣናቸው የሚቆዩበትን የህገመንግስት ለውጥ ማጽደቃቸው ይታወሳል።
በህገመንግስታዊ ድንጋጌ ለውጡ መሰረትም አል ሲሲ ግብፅን እስከ 2030 ድረስ መምራት የሚችሉበት እድል መፈጠሩ ነው የተገለጸው።
ይህን ተከትሎም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን ግብጻውያን ትናንት ህዝበ ውሳኔ አድርገውበታል። በህዝበ ውሳኔው ድምፅም የፕሬዚዳንት አል ሲሲን በስልጣን እንዲቆዩ የሚፈቅደውን ድንጋጌ አብዛኛው ህዝብ ደግፎታል ነው የተባለው። ህዝብ ውሳኔ ማካሄድ ከሚጠበቅበት 61 ሚሊየን ህዝብ ውስጥ ድምፅ የሰጠው 27 ሚሊየን ወይም 44.33 በመቶ ብቻ ነው። ድምፅ ከሰጠው ህዝብ ውስጥ 88.83 በመቶዎቹ ህገመንግስታዊ ማሻሻያውን የደገፉ ሲሆን 11. 17 በመቶዎቹ ደግሞ መቃወማቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። የግብፅ ፓርላማ ያደረገው ህገመንግስታዊ የድንጋጌ ለውጥ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ለአንድ ዙር በስልጣን የሚቆዩበትን የአራት ዓመት ገደብ ወደ ስድስት ዓመት ከፍ አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ከሆነ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ሀገሪቱን የመምራት እድል ፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው። ምንጭ፦ሬውተርስ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም