የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ነው—የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

2049

ሀዋሳ ግንቦት 27/2010 የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የጤናው ዘርፍ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ መዋቅሮች የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ  ተጀምሯል፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ለሃርሳ አብዱላሂ እንገለጹት ሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ እድገትና ለውጥ እያስመዘገበች ነው፡፡

ይህንን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ  የሴቶችን፣ ወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በጤናው መስክ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት የግብዓት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ለዘርፉ ስራ ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ፍላጎታቸውን ማዕከል ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥና ተጠያቂነት ስርዓት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“ወጣት ተኮር አገልግሎት አሰጣጥ በመደበኛው የጤና ተቋማት እየተሰጠ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ የጤና መረጃዎች፣ አገልግሎቶችና ተደራሽነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስፋፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ እንዳሉት የሚገነቡ የጤና መሰረተ ልማቶች  የአካል ጉዳተኞችን በተለይም የእንቅስቃሴ ጉዳት ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

በየደረጃው የተቋቋሙ የሴቶች ልማት ቡድን አደረጃጀቶች ትግበራ በማሻሻል የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት መቀነስ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋጥ በቀጣይ ትኩረት ይደረግበታል፡፡

መድረኩ የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከጤና አገልገልሎት አሰጣጥ ጥራትና ፍትሃዊነት እንዲሁም ሩህሩህ አገልጋይ ከመፍጠር አኳያ የተሰሩ ስራዎች የሚገመገምበት ነው፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በበኩላቸው በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ ለተመዘገቡት ስኬቶች የሴቶች የተጠናከረ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ መሆናቸው በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተገቢውን ግብዓት ማግኘት እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሃም አላኖ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ የክልሉን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

“የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ በአብዛኛው ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን በቀላሉ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለወጣት ሴቶች የስራ እድል የፈጠረ ነው” ብለዋል፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግባራ ዘመናትም ዋና ትኩረት የጤና አገልግሎቱ ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሴቶች የልማት ቡድን ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ በማድረግ የክልሉን በጤና ተቋም የመውለድ ምጣኔ 77 ከመቶ ማድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ባለፉት አስር ወራት በሁሉም ክልሎች በሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች የጤና ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ላይ የተከናወኑ ተግባራት ይገመገማሉ፡፡

እስከ ሰኔ 2/2010ዓ.ም በሚቆየው መድረክ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚመላከት የሚጠበቅ ሲሆን የፌደራልና የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡