የጌዴኦ ዞን ተፈናቃዮችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው

56
ሚያዝያ 15/2011 የጌዴኦ ዞን ተፈናቃዮችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ፡፡ የጌዴኦ ዞን ተፈናቃዮችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ፡፡ ችግሩን ለመግታት የምግብ ስርጭቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፍቅሩ በደቻ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈናቃዮቹን ጤና ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተቀናጀ  እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው። በዚህም የሥርዓተ ምግብ ልየታ፣ የንጸህና ቁጥጥርና የተላላፊ በሽታዎች ዳሰሳና ቅኝትን ጨምሮ በስድስት መስኮች በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። በተለይም ህጻናት፣ ነብሰ ጡርና አጥቢ እናቶች ለበሽታ እንዳይጋለጡ በተለየ ትኩረት በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ካለፈው ወር ጀምሮ ከ15ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለመካከለኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናት ይዘቱ ከፍተኛ አልሚ ምግብ በማሰራጨትና የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ 2ሺ353 ህጻናት ተለይተው የውሎ ገብ አንዲሁም 357 ህጻናት በተወሳሰበ የጤና እክል የዲላ ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ በዞኑ ጤና ተቋማት ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከዞኑና ከአጋር ድርጅቶች የተውጣጡ 228 የጤና ባለሙያዎች ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው አካባቢዎች በተቋቋሙ 13 የጤና ማዕከላት ውሎ በማደር የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ ከሥርዓተ ምግብ ልየታ ውጭ የሆኑ 82 ሺህ ዜጎች የጤና አገልግሎት መሰጠቱን አቶ ፍቅሩ  ገልጸዋል። በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙ ህጻናትና እናቶች ለከፋ የጤና እክል እንዳይዳረጉ መደበኛው የምግብ ስርጭት መቅረብ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ የዲላ ሪፈራር ሆስፒታል የህክምና ቡድን መሪ ዶክተር ተስፋነው በቀለ በበኩላቸው በገደብ ሆስፒታልና በመጠሊያ ጣቢያዎች በተቋቋሙ የጤና ማዕከላት ለተፈናቃይ ወገኖች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ ለወረርሽኝ ስለሚያጋልጥ አገልግሎቱን ማጠናከር ወሳኝነት አንዳለው አመልክተዋል። በተወሳሰበ የጤና እክል በገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ከሚገኙት መካከል ወይዘሮ ብርቱካን ተሰማ እየተደረገላቸው በሚገኘው የህክምና ድጋፍ የልጃቸው ጤንነት መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ ወተትና አልሚ ምግብ በተከታታይ በማግኘቱ አንድ ሳምንት ውስጥ ለውጥ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ለእናቶች የምግብ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ አልሚ ምግቦች በሁሉም ወረዳዎች መከማቻተቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም