ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ - የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

113
ሚያዝያ 14/2011 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ እንዲሁም ከኦሮሚያ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት "የፖለቲካ ጥቅም  በሚሰሩ ጥቂት አሻጥረኞች" በተቀነባበረ  ሴራ ነው። "በምንም ምክንያት ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ማየት አሳዛኝ ነው" ያሉት ሃላፊው የኦሮሚያ ክልል የመኸር እርሻ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮቸን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል። በመሆኑም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ኦሮሚያ ፣ ከጉጂ ዞን ወደ ደቡብ ክልል እንዲሁም  ከጌዴኦ ወደ ጉጂ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ ይከናወናል ብለዋል። የክልሉ መንግስት ከፌዴራል እና ከአጎራባች የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስታት ጋር ዜጎችን መመለስን በተመለከተ ሰፊ ውይይት አድርጎ መግባባት ላይ ተደርሷልም ነው ያሉት። በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ  አብዲሳ የሚመራ ልኡክ ከጉጂ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ ዜጎችን በሚመከት ከደቡብ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንም አውስተዋል። ከያዝነው ሳምንት ጀምሮም ተፈናቃዮቹን ወደ ኦሮሚያ የመመለሱ ስራ ይጀመራል ብለዋል። ክልሉ ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስም የዘር አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠዋል። ዜጎች በሚመለሱበት ጊዜ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንዳይፈጠርባቸው በጸጥታ በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል። በቀጣይም መሰል ችግር እንዳይፈጠር የኢፌዴሪ መንግስት በትኩረት ክትትል እንደሚያደርግ ቃል እንደገባላቸው አውስተዋል። የኦሮሚያ ክልል  ከሌሎች ክልሎች በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች በጋራ የሚለሙባቸው መሰረተ ልማቶችን  በመገንባት ለዜጎች አብሮነት የበኩሉን እንደሚወጣም አውስተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም