በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የእርስበርስ ንግዱንና የግሉን ዘርፍ ማጠናከር ወሳኝ ነው

90
አዲስ አበባ ሚያዝያ 14/2011  በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የእርስበርስ ንግዱንና የግሉን ዘርፍ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። በምክር ቤቱ አዘጋጅነት የአፍሪካ አለም አቀፍ የንግድና ኢኮኖሚ ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል። በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የግሉን ዘርፍ፣ የፖለቲካ መሪዎች በመቀናጀት በአገራቱ መካከል ያለውን የእርስበርስ ንግድ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል። የምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጥ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካዊያን የኢንቨስትመንትና ንግድ እንቅስቃሴ እየጨመረ ቢሆንም በመካከላቸው ያለው የንግድ ትስስር ሲታይ አሁንም እዚህ ግባ የማይባል ነው ብለዋል። ለዚህም የፖለቲካ መሪዎች ለእርስበርስ የኢኮኖሚ ትስስሩ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራትና ከእርስበርስ ንግድ ይልቅ ከሌሎች አህጉር አገራት ጋር ላለው ትስስር ትልቅ ሚዛን የመስጠት ችግር ይታያል ብለዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ ያለውን የእርስበርስ የኢኮኖሚ ትስስር ምቹ ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ሲጠቀምበትም አይታይም ሲሉም አስረድተዋል። በመሆኑም ይህን ክፍተት ለማስተካከል በፖለቲካ መሪዎቹ በኩል ለኢኮኖሚ ትስስሩ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር፣ የግሉን ዘርፍ ማጠናከርና ማጎልበት እንዲሁም የገንዘብ ተቋማትን ማጠናከር የግድ ይላል ሲሉ ተናግረዋል። በአፍሪካ ህብረት የንግድ ኮሚሽነር ሚስተር አልበርት ሙቺንጋ በበኩላቸው በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት፣ የመሰረተ ልማት፣ የተማረና ወጣት የሰው ሃይል እድገት ፈጣን መሆኑ እንደ አንድ እድል ቢሆንም አሁንም ያልተወጣናቸው ብዙ ስራዎች አሉ ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አገራቱ በውስጣዊ አሰራራቸው መተግበር ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም የጋራ ነፃ ገበያንና እንደአጠቃላይ የኢኮኖሚ ትስስርን ሊያጠናክር የሚችል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት በኩል ግን ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።  በአገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስርና ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ ለማጎልበት የገንዘብ ተቋማትን ማጠናከርና የብድር ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ዋና መሆኑንና ለዚህም የህብረቱ አገራት የፈረሙበት የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም የሚያስችቭል የህግ ማዕቀፍም ተዘጋጅቷል።     የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእርስበርስ ትስስሩን ለማጎልበት ትልቅ ሚና ከሚወጡት አገራት መካከል መሆኗንና ለረዥም አመታት እየሰራችበት ያለው አጀንዳ ነው ብለዋል።   ለዚህም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ሪፎርም የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የአፍሪካ አገራትን የንግድ ትስስር ከግምት ያስገባና ከግብ ለማድረስም ያለመ ነው ሲሉ ገልጸዋል።   የእርስበርስ የነፃ ገበያ ትስስሩ መጠናከር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም መሳካት የራሱ ሚና አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም የስራ እድል ከመፍጠር፣የግሉን ዘርፍ ከማጠናከርና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ ጥሩ ሂደት ላይ ነን ሲሉ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም