አዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ ሁሉንም በእኩልነት ማስተናገድ የሚችል እንዲሆን ተጠየቀ

136
ሚያዝያ 14/2011 አዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ ሁሉንም በእኩልነት ማስተናገድ የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲካተቱበት ተጠየቀ። አዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ የግልና የመንግስት ተቋማትን በእኩል ማስተናገድ በሚችል መሆን እንዳለበት ተጠየቀ። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከመንግስትና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አካሂዷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ላይ ብቃት ያላቸውን መምህራን እጥረት በዘርፉ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አንዱ ነው። በመሆኑም በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል አንቀጽ እንዲካተት ጠይቀዋል። በዘርፉ በርካታ አመታት የዘለቁ፣ ውጤቶችን ላስመዘገቡ የተለያዩ መመዘኛዎችን በማስቀመጥ የመሬት አቅርቦትን የማሟላት ግዴታ ቢቀመጥም ብለዋል። ተቋማቱ በዝግ ተቀማጭ ሂሳብ 500 ሺህ ብር ተቀማጭ እንዲያደርጉ ግዴታ የሚያስቀምጠው አሰራር ባለ ሀብቶች ብቻ በዘርፉ እንዲሰማሩ እንጂ ምሁራን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ በመሆኑ ይህን አሰራር ማስቀረት ይገባዋል ብለዋል። የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ፣ የተቋማት ወደ ኮሌጅና ዩንቨርስቲ ዕድገት ጥራትን ያማከለ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበት አሰራርም መመቻቸት አለበት ብለዋል። በግል ተቋማት የተማሪዎች የወጪ መጋራት አሰራር፣ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እና ሌሎች በአዋጁ እንዲካተቱም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። አዋጁ ለግሉ የትምህርት ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት የሰጠና ለመንግስት ተቋማት ብቻ ሳያዳላ የዘርፉን ተቋማት በእኩልነት የሚመለከት ሊሆን ይገባልም ብለዋል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያለው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ለአስር አመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በትግበራ ወቅት በርካታ ችግሮች ያጋጠሙ በመሆኑ ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል። የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው በ1995 ዓ.ም ሲሆን በተደጋጋሚ ማሻሻያ ሲደረግበት መቆየቱንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ መልክ እየተዘጋጀ ያለውን የትምህርትና የስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት መሰረት በማድረግ በርካታ ማሻሻያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የመንግስትና የግል ተቋማት መምህራንን በጋራ መቅጠር በተመለከተ ከግል ተቋማት ሃላፊዎች ለተነሳው ጥያቄም  በመንግሰት በጀት የተቀጠረ መምህርን በግል ተቋም በጥምር እንዲቀጠር መፍቀድ መንግሰት መቆጣጠር የማይችለው የሰው ሀይል እንዲኖር መንገድ የሚከፍት በመሆኑ  ይህንን መፍቀድ የሚቻልበት አቅም ላይ  አልደረስንም  ብለዋል። የመሬት አቅርቦት በተመለከተም እራሱን የቻለ አዋጅ በመኖሩ በትምህርት አዋጅ ላይ ማካተት አስፈላጊ አይደለም ነው ያሉት። እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ ለመንግስት ሳያሳውቁ ኮሌጆችን የሚዘጉና ተማሪዎችን የሚበትኑ ተቋማት በመኖራቸው ኮሌጆች ሲዘጉ ተማሪዎችን የማዘዋወርና ሌሎች ወጪዎችን በመንግስት ሲሸፈን ቆይቷል። ይህንን ችግር ለመፍታትም መንግስት መተማመኛ የሚያስፈልገው በመሆኑ ኮሌጆች በዝግ ተቀማጭ ሂሳብ 500 ሺህ ብር ተቀማጭ እንዲያደርጉ ያስፈለገው ብለዋል። የመንግስት ተቋማት በህዝብ ሀብት የሚቋቋሙ በመሆኑ በእኩልነት በህግ እንዲደገፉ መጠየቅ ምክንያታዊ አለመሆኑን ገልጸው ለመንግስት ተቋማት አድሎ እንደተደረገ ማየት ተገቢ አይደለም ሲሉም አብራርተዋል። የግል ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት በሚያከነውኗቸው ስራዎች ላይ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን አቅም ይዘው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም