በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

44
ሚያዝያ 14/2011 በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በማህበር ለተደራጁና መኖሪያ ቤት ለሌላቸው ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስርያ ቦታ ተሰጠ። የከተማው  ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋይ ወልደምህረት ትናንት በመሬት እደላው ስነ ሰርዓት ላይ እንዳሉት ፣ በ52 ራስ አገዝ ማህበራት ለተደራጁ አንድ ሺህ 40 ሰዎች በነፍስ ወከፍ 70 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷል። በተጨማሪም በማህበር የተደራጁ 500 መምህራንና የትግራይ የጦር አካል ጉዳተኞች ማህበር አባላት እያንዳንዳቸው 140 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲረከቡ ተደርጓል። የእርሻ መሬታቸው ለመኖሪያ ቤት መስርያ የተወሰደባቸው 163 አባወራና እማ ወራዎችም በነፍስ ወከፍ 500 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጣቸው የገለጹት አቶ ተስፋይ፣  ለአቅመ አዳም የደረሱ 483 የአርሶ አደሮቹ ልጆችም ለያንዳንዳቸው 140 ካሬ ማትር ቦታ መሰጠቱን ጠቁመዋል። በከተማው ትናንት በተከናወነው የቦታ እድላ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዕርግ የትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ የክልሉን ከተሞች ትክክለኛ እድገት ማረጋገጥ የሚችሉት የክልሉን የመሬት ፖለሲ በአግባቡ ሲተገብሩ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። "ከክልሉ የመሬት ፖሊሲ ውጭ የሚደረጉ የመሬት ወረራና ህጋዊ ያልሆነ ግንባታ ከተሞቹን ወደ ግርግርና ሁከት ከማምራት ውጭ ፋይዳ የለውም " ብለዋል። ከተሞቹ ባላቸው ማስተር ፕላን መሰረት ሁሉንም የመሰረተ ልማቶች፣ የመኖሪያ ቤትና የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ማካሄድ ለእድገታቸው መፋጠን እንደሚያግዛቸውም አስታውቀዋል። ከተሞቹ በፕላን ተመርተው እንዲሰፉና ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ የነዋሪዎች ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ገልጸው ለከተሞቹ ጤናማ እድገት ነዋሪዎች ከመስተዳድር አካላት ጎን መቆም እንዳለባቸው አመልክተዋል። በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት ያገኙት ወገኖችም ህግ በሚፈቅደው መሰረት  እንዲያለሙ ነው የቢሮ ኃላፊው ያሳሰቡት። መሬቱን የተረከቡ ዜጎች መሬቱን አልምተው ለመጠቀም በጥንካሬ መንፈስ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገ የገለጹት ደግሞ የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ናቸው። የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት ካገኙት መምህራን መካከል መምህር እያሱ እስቅያስ የዓመታት የመሬት ጥያቄያቸው በመመለሱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለ20 ዓመታት በቤት ኪራይ መኖራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ትርሓስ ብርሃነ በበኩላቸው፣ “የቤት መስሪያ መሬት በማግኘቴ ዳግም ሕይወቴ እንደለመለመ ነው የምቆጥረው” ብለዋል። በከተማው በመጀመሪያ ዙር ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ተመሳሳይ የመሬት እድላ መካሄዱን መገለጹ ይታወሳል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም