ከዳንግላ ጃዊ እየተሰራ ያለው የጠጠር መንገድ ዋሻ ውስጥ ከማደር አላቆናል …የአካባቢው ነዋሪዎች፡፡

174

ባህር ዳርሚያዝያ 14 /2011 .ከዳንግላ ጃዊ እየተሰራ ያለው የጠጠር መንገድ ዋሻ ውስጥ ከማደር አላቆናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እየተገነቡ ያሉት የዳንግላ ጃዊ የጠጠር መንገድና የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንግድ ግንባታ ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ የዳንግላ ወረዳ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአቅራቢያቸው ካሉ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለዘመናት ተለያይተው ከሚኖሩበት ሁኔታ በመንገዱ መገንባት ምክንያት መገናኘት ችለዋል።

በወረዳው ወንዲፋይ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር አሻግሬ ቢሻው እንዳሉት ቀደም ሲል አካባቢው ተራራማ በመሆኑና መንገድ ባለመዘርጋቱ እርስ በእርስ ለመገናኘት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“በተለይም ከጃዊ አዋሳኝ ቀበሌዎች ጋር ለመገናኘት አስቸጋሪ የሆነውን ተራራማ ቦታ መውጣትና መውረድ ባለመቻሉ ዋሻ ውስጥ እስከ ማደር ይደረስ ነበር” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ተራራውን በመቁረጥ እየተሰራ ያለው መንገድ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ አጎራባች ቀበሌዎች ደርሶ ለመመለስ ማስቻሉን ጠቁመው ” መንገዱ የደጋውንና  የቆላውን ዘመድ በጋራ ቡና እስከመጠጣት አድርሷል” ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለዘመናት ፈላጊ አጥቶ የነበረውን ባህር ዛፍና ገለባ በመሸጥ ገቢ እያገኙ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

በመንገዱ ግንባታ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል።

 የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደር አወቀ ይሁኔ በበኩላቸው በፊት ተራራን አቋርጦ ከመሄድ ጋር ተያይዞ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

“በአሁኑ ወቅት ተራራውን ከሁለት በመክፈል በተሰራው መንገድ በደስታም ሆነ በሃዘን ስንለያይ የነበረ የሁለቱ ወረዳ ህዝቦች ልንገናኝ ችለናል” ብለዋል፡፡

በመንገዱ ግንባታ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው በመስራታቸው እሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

አርሶ አደር የዓለም አዲስ በበኩላቸው የመንገዱ መሰራት በቀን ሥራ ተቀጥረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረጉ በላይ ለረጅም ጊዜ ችግራቸው የነበረው የመንገድ እጦት መፍታቱ እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል።

የዳንግላ ጃዊ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማው ምንውየለት በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክቱ በ891 ሚሊዮን ብር ወጭ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

63 ኪሎ ሜትር የሆነው የመንገዱ አካል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ የመንገዱን ግንባታ ሥራ 86 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ቀሪው 7 ኪሎ ሜትር አስቸጋሪ ተራራ ያለበትና ከ30 እስከ 70 ሜትር ከፍታ የተራራ ቆረጣ ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የመንገዱ መገንባት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የዳንግላና ጃዊ ወረዳዎችን ጨምሮ ሌሎች  የአካባቢው ወረዳዎችንና ቀበሌዎችን እርስ በእርስ ለማገናኘት ማስቻሉን ተናግረዋል።

የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አለማየሁ በበኩላቸው ድርጅቱ 687 ኪሎ ሜትር የጠጠርና የአስፓልት መንገዶችን ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዳንግላ ጃዊ፣ የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ፣ ከፍቼ ጎሃ ጺዎን አስፓልት ማንጠፍ ስራን ጨምሮ 14 ፕሮጀክቶች በድርጅቱ በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።፡

በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እየተገነቡ ያሉት የዳንግላ ጃዊ 70 ኪሎ ሜትርና የቡሬ ፓርክ 11 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራዎች አስቸጋሪና ውስብስብ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱንም የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘው  በጀት ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል።

የሁለቱን መንገዶች ግንባታ በባለድርሻ አካላትና በተቋሙ ሠራተኞች መጎብኘቱ   ታውቋል፡፡