ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ጊዜ፣ጥበብና ብልሃት ይፈልጋሉ- የኦሮሚያና አማራ ክልል መሪዎች

209

ሚያዝያ 14/2011 በየጊዜው የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እርጋታ፣ጥበብና ብልሃት እንደሚያስፈልግ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።

በየጊዜው የሚነሱ አጀንዳዎችና ህዝባዊ ጥያቄዎች ጊዜ የሚፈልጉ፤ በጥበብና ብልሃት የሚፈቱ መሆናቸውን የአማራ ክልልና  የኦሮሚያ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።

በተለያ ጊዜያት የሚነሱ የህዝብ ጥያዌዎችን በዘላቂነት ለመመለስ የተቋም ግንባታ ላይ አበክሮ መስራት  ያስፈልጋል ብለዋል።

በአምቦ ከተማ በተደረገው የኦሮሞና የአማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጉባኤ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ርዕሳነ መስተዳድሮቹ  ምላሽ ሰጥተዋል።

ከጥያቄዎቹ መካከል  ስለአዳዲስ አመራሮች ቀጣይ የትብብር ምዕራፍ፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የጎሰኝነት ጉዳይ፣ በህዝቦች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችና የህግ የበላይነት ጉዳይና ሌሎችም ይገኙበታል።

 የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት፣  የጥበብ ውጤቶች ባለቤት፣ የሰላም ወዳድ ህዝቦች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ይህንን ለማስቀጠል የህዝቦች ትብብር አማራጭ የለውም ብለዋል።

 “እኛ መሪዎች ድርሻችን የመምራት ነው፤ታሪክ ሰሪዎች እናንተ ህዝቦች ናችሁ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ  ህዝቡ በታሪካዊቷ አገር ላይ ሌላ ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት ይኖርበታልም ነው ያሉት።

 “የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ህዝቦች ከሁለቱም ወገን ያሉ አመራሮች ተቀራርበው እንዲሰሩ ተጽዕኖ መፍጠር ትችላላችሁ” ያሉት ዶክተር አምባቸው የሁለቱን ክልል አመራሮች ለመከፋፈል የሚደረጉ    የፖለቲካ የአክቲቪሰት ሞገዶች ቢገጥሙም ህዝቡ ሊታገላቸው ይገባል ብለዋል።በየወቅቱ አጀንዳ እየቀረጹ በመሪዎች ስም ለማበጣበጥ ለሚጥሩ ሃይሎች ህዝቡ ጉዳዩ የወሬኞችና የሴረተኞች አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ መገመት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሄረሰብ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ተረጋግተው፤ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርና ዜጎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና ዳግም ችግር እንዳይከሰት  እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

‘የወቅቱን ማህበረስብና የተደረጃ ወጣት መምራት ከባድ ነው’ ያሉት ዶክተር አምባቸው፤ የህዝብ ጥያቄዎቸን በስሜት ሳይሆን በጥበብና በብልሃት መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከወቅታዊ ጥያቄዎች የአዲስ አበባን ጉዳይ ያነሱት ዶክተር አምባቸው የአማራ ክልል መንግስት የኦሮሚያ ክልል   በአዲስ አበባ ላይ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን መብት የሚሸራርፍ አቋም የለውም ብለዋል።

ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበር እንደሚደግፉ ገልጸው፤ ‘ከዚህ ውጭ ያሉት ጽንፈኛ አሰራሮች ግን ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በየቦታው የሚነሱ ችግሮችና     ጥያቄዎች ለመመለስ ጊዜና የተረጋጋ ጥበብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በአቶ ገዱና በአቶ ለማ የተጀመረው የአማራና ኦሮሞ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር በመካከል የነበሩ ችግሮች መስመር መስመር መያዛቸውንና ግንኙነቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ለሁለቱም ክልል ህዝቦች ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና እድገት በትኩረት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

ህዝቦች በታሪክ ሂደት ውስጥ የአንድነት ችግር የለባቸውም ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤      ችግሩ የሊሂቃንና ፖለቲከኞች በቡድን ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚፈጥሩት ጉዳይ ነው ብለዋል።

‘በታሪክ የነበሩ ህጸጾችም የህዝብ ችግሮች አይደሉም፤ ባለፈ ታሪክ መማር እንጂ የምንቆዝም ከሆነ እንደህዝብ ወደ ፊት መራመድ አንችልም’  ብለዋል አቶ ሽመልስ።

በቀጣይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ሌላ ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት እንደሚሻም ገልጸዋል።

‘ኢትዮጵያ የኢያሪኮ ግንብ አይደለችም፤ በጩኸት አትፈረሰም’ ያሉት አቶ ሽመልስ በወሬ  ማንም ሊያፈርሳት እንደማይችል ህዝቡ መገንዘብ ይኖርበታል ብለዋል።

ህዝቡ በየትኛውም አይነት አስተሳስብ መደናገር የለበትም፣ ጥያቄው እያንዳንዳችን ለዚህች አገር ቀጣይ እጣፈንታ ምን ጡብ እናስቀምጥ የሚል ሃላፊነት መውሰድ ይገባልም ነው ያሉት።