አርቲስት ወይኒቱ አንዱር ባህልን በማስተዋወቅ እውቅና ተሰጣት

267

ሚያዝያ 14/2011 አርቲስት ወይኒቱ አንዱር የህብረተሰቡን ባህል ከአካባቢው አልፎ ለዓለም በማስተዋወቅ ላበረከተችው  አስተዋጽኦ “የባህል አምባሳደር” በሚል እውቅና ተሰጣት፡፡

አርቲስቷ ዕውቅና ሽልማቱ የተሰጣት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በግልገል በለስ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሶስተኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህል ሳምንት ላይ ነው፡፡

በቀድሞው ምዕራብ ጎጃም ዞን ወምበርማ ወረዳ የተወለደችው አርቲስቷ ባህላዊ ሙዚቃን የጀመረችው በ1970 ዓ.ም.  እደሆነ ነው ለኢዜአ ገልጻለች፡፡

በራስ ቲያትር፣ ሀገር ፍቅር ቲያትርና በሄራዊ ትያትር ለረጅም ዓመታት ከእነ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ና ሌሎችም ታላላቅ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ሠርታለች፡፡

አርቲስቷ በተለይም ተወዳጅነትን ካተረፈችባቸው ሙዚቃዎቿ መካከል “አንበሳ ዊያ ” ወይም “አንበሳው መጥቷል” በሚለው ለብሔረሰቡ ጀግኖች በሚዜመው የጉሙዝ ባህላዊ ዘፈኗ ትታወቃለች፡፡

ከጉሙዝኛ በተጨማሪ በአማርኛ፣ አገውኛና ሌሎችም ቋንቋዎች ሥራዎቿን በሃገር ውስጥ እንዲሁም በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና አፍሪካ የተለያዩ ሀገራት አቅርባለች፡፡

በትላንቱ የባህል ሳምንት ዝግጅት ላይ ይህቺው አርቲስት የሃገሯን ባህል ለዓለም በማስተዋወቅ ላበረከተችው አስተዋጽኦ “የባህል አምባሳደር” እውቅናና የካባ ሽልማት ከክልሉ መንግስት አግኝታለች፡፡

አርቲስት ወይኒቱ በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ህይወት እንደምትኖር በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

እውቅናውን ያበረከቱላት የክልሉ ምክትል ርዕሰ ስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በክልሉ መንግስት የ50 ሺህ ብርና በግልገልበለስ ከተማ የንግድ ቦታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

አርቲስቷ የክብር ሽልማቱ ከተበረከተላት በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ በስፋት የምትታወቅበትን “አንበሳ ዊያ” የተሰኘውን በማቀንቀን የባህል ሳምንቱ ታዳሚዎቿን ያዝናናች ሲሆን ተመልካቹም ለእርሷ ያላትን ፍቅርና አክብሮት ገልጿል፡፡

ህዝቡ ለሰጣት ፍቅርና ለተበረከተላት እውቅና ምሥጋና አቅርባለች፡፡

በ60ዎቹ ዕድሜ የምትገኘው አርቲስት ወይኒቱ አንዱር ከእድሜ መግፋትና ሌሎችም ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ከሙያው መራቋን ለማወቅ ተችሏል፡፡