ምሁራን በግብርና ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩን እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ

440

አዲስ አበባ ሚያዚያ 14/2011 ኢትዮጵያውያን ምሁራን የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማፍለቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

አቶ አክሊሉ አባተ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራችውን ባለሞተር ማረሻ በመፍጠር በተለይም ለአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ ገበሬዎች አበርክተዋል።

በመካኒክነት ሙያ 40 ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ አክሊሉ በግብርና ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም ድረስ ከበሬ ትከሻ አለመላቀቁ እንደሚያሳስባቸውም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በሙያቸው የድርሻቸውን ለመወጣት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለይም ለአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚዎች ለማረሻ፣ ማጨጃ፣ መድሃኒት መርጫና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ትራክተር ሰርተዋል።

በኢትዮጵያ ከዛሬ 3 ሺህ ዓመት በፊት ይታረስበት የነበረው በሬ አሁንም ወደ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመቀየሩ የሚያስቆጭና የባለሙያዎችን ትኩረት የሚሻ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።

በባለሙያ፣ በመንግስትና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ከተለያዩ አገሮች የምናስገባውን የግብርና ግብዓትና መሳሪያ ኢትዮያውያንም እንደ አደጉት አገሮች መስራት እንደምንችል ማሳየት አለብን ሲሉም ይመክራሉ።

አሁን ባለው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት 24 ሚሊዮን ተመሳሳይ ባለሞተር ማረሻ ትራክተር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ አክሊሉ “እኔ በህይወት ዘመኔ 10 ሺህ ሰርቼ ባልፍ ለአገሬ ትልቅ ነገር ነው” በማለት ይናገራሉ።

ወጣት ነብዩ ጌታቸው በመካኒካል ኢንጅነሪንግ የተመረቀ ባለሙያ ሲሆን ከኢንጅኗ ውጪ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ የተሰራችውን ማረሻ ትራክተር ይዞ ቀርቧል።

ወጣት ነብዩ በትምህርት ቆይታውም ቢሆን ግብርናውን ለማዘመን የተለያዩ ማሽኖችን ለመስራት ፍላጎት እንደነበረው ገልጾ በቀጣይም ሌሎች የፈጠራ ውጤቶችን ለማበርከትም ህልም አለው።

በከፍተኛ ትምህርት ቆይታው ለአገራቸው ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማበርከት የሚችሉ ምሁራን መኖራቸውን መታዘቡን በመጠቆም በተለይም ወጣቶች አገራቸውን ለመቀየር በእውቀታቸው እንዲያግዙ ጠይቋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ይበልጣል መኮንን ከቴክኒክና ሙያ ባገኘው እውቀት ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ለምርት ማጨጃና መውቂያ የሚያገለግሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ለመስራት በጅምር ላይ ናቸው።

“ኢትዮጵያውያን ተባብረን የአገራችንን ግብርና ማዘመን አለብን” የሚለው ወጣት ይበልጣል በቴክኖሎጂ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎች፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ እየተመረቁ ቢሆንም ተግባር ላይ ግን አሁንም ገና መሆናቸውን ያነሳል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው “እስከዛሬ ድረስ ቴክኖሎጂ ማወቃችንና መማራችን ጥሩ ቢሆንም ገበሬዎቻችንን በዘርፉ አልደገፍናቸውም” ብለዋል።

በማረሻ ቴክኖሎጂ ገበሬዎች ባለመደገፋቸው እስከዛሬ ድረስ ከበሬ የተላቀቀ ግብርና መፍጠር አለመቻሉን ገልጸው አገራዊ የሆነውን ችግር አገራዊ በሆነ ቴክኖሎጂ ለመፍታት መሰራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

“እውቀታችን ለህዝብ ካላደረስን የምናፍርበት እንዳይሆን” በማለት ምሁራን በሙያቸው አገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ምሁራን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄዱና የገበሬውን አቅም ያገናዘቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲያበረክቱ ጠይቀው የኢኖቬሽንናቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመስኩ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እንደሚሉት ግብርናውን ለማዘመን መንግስት ከውጭ አገራት የማረሻ ትራክተርን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እያስገባ ቢሆንም ከአገሪቷ መሬት ጋር አብረው የሚሔዱ ባለመሆናቸው የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ካለው 100 ሚሊዮን ህዝብ 24 ሚሊዮን የሚሆነው አርሶ አደር አባወራና እማወራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።