በትግራይ ክልል በየዓመቱ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በኤች. አይ. ቪ/ኤድስ ይያዛሉ….የክልሉ ጤና ቢሮ

347

ሚያዝያ 14/2011 በትግራይ ክልል በየዓመቱ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በኤች. አይ.ቪ/ኤድስ በአዲስ መልክ እንደሚያዙ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ቀደም ባሉት ዓመታት በተለያዩ አካላት በሽታውን ለመከላከል የነበረው መነሳሳትና ሲከናወኑ የነበሩ ሥራዎች እየቀነሱና እየተቀዛቀዙ መምጣታቸው ስርጭቱ በወረርሽኝ መልክ እንዲስፋፋ ማድረጉም ተመልክቷል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መቆጣጠርና መከላከል የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ በሪሁ መስፍን ለኢዜአ እንዳሉት በሁሉም ባለድርሻ አከላት ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መጥቷል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጎ አድራጊ ተቋማት የሚመድቡት በጀት መቀነሱ አንዳንዶቹም ማቋረጣቸው ለበሽታው አየተስፋፋ መምጣት ሌላው ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት።

ቫይረሱ በደማቸው ባለባቸው ሰዎች የተቋቋሙና ሕብረተሰቡን ሲያስተምሩ የነበሩ ማህበራት እየፈረሱ መምጣታቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች የሚሰጡት ትምህርት መቀነሱና በህብረተሰቡ ላይ በሽታው የለም የሚል የተሳሳተ አመለካከት እያደገ መምጣት ለስርጭቱ መስፋፋት ከሚጠቀሱ ተጨማሪ ምክንያቶ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ የበሽታው ስርጭት እያደገ በመምጣቱ በየዓመቱ በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ  800 በላይ መድረሱን አመልክተዋል።

“ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምክርና የምርመራ ሥራ አለመሰራቱም የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር አድርጓል” ብለዋል አቶ በሪሁ።

እንደእርሳቸው ገለጻ በትምህርት ቤቶችና  በየቢሮው የነበሩ የጸረ ኤች አይቪ/ የኤድስ ክበባት መዳከማቸው የበሽታው ስርጭ ዳግም እንዲያንሰራራ ዕድል ፈጥሯል።

የአነስተኛ ከተሞች መስፋፋት እንዲሁም በየመጠጥ ቤቱ ጭፈራ ቤቶችና ወጣቶችን ለሱስ የሚዳርጉ ቦታዎች መበራከት ለስርጭቱ መስፋፋት አስዋጽኦ ማድረጋቸውን ነው የጠቆሙት።

የብሩህ ተሰፋ ጸረ ኤድስ መከላከያ ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ መልክአ አስገዶም በበኩላቸው ከጤና ቢሮ ይደረግላቸው የነበረው ድጋፍና ክትትል በመቋረጡ አቅማቸው መዳከሙንና ሕብረተሰቡን ማስተማር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል እየቀነሰ የነበረው የኤች አይ ቪ/ ኤድስ በሽታ በአሁኑ ወቅት ዳግም እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

“በሆቴሎችና ቡና ቤቶች ቀደም ሲል በነጻ ሲከፋፈሉ የነበሩ ኮንደሞች መቋረጣቸው ለበሽታው መስፋፋት የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ናቸው” ያሉት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የቀዳማይ ወያነ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታምራት የማነ ናቸው።

በኮንደም ስርጭት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ በሪሁ መስፍን ኮንደም በበቂ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው ስርጭት ላይ በሆቴሎችና ቡና ቤቶች የሚታየውን ችግር ለመፍታት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ቢሮዎች ከበጀታቸው 2 በመቶ ቫይረሱን ለመከላከል ለመመደብ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም  ገልጸዋል።

በክልሉ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ከ64 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።