አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በጥረት ኮርፖሬት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው

388

ሚያዝያ 14/2011 የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በኮርፖሬቱ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት አራት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ክሳቸውን በንባብ አሰምቷል፡፡

ተከሳሾቹ የህዝብ ሃብት የሆነውን ጥረት ኮርፖሬትን መጠበቅና በትክክል ማስተዳደር ሲገባቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ከደንብና መመሪያ ውጭ ውሎች ፈፅመዋል፡፡

በዚህም በአንደኛ ክስ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማምረትም ሆነ የገበያ አቅም እያለው ተገቢ ጥናት ሳይካሄድ ለእንግሊዙ ዱየት ቢቬሬጅ ፋብሪካ ድርሻውን 50 ነጥብ 14 በመቶ በመሸጥ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

በዚህም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲባል በፋብሪካው ላይ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በሁለተኛ ክስ ዱቬንቱስ ዊንድ ከተባለ የግል ኩባንያ ጋር የመብራትና የውሃ ቆጣሪ እዲያመርት የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ ከህግ አግባብ ውጭ በመዋዋል ጉዳት ማድረስ ችለዋል፡፡

በዚህም ለባንክ ጋራንት በመስጠት፣ ለፋብሪካ ግንባታ ኪራይ፣ ለህንፃ ጥገናና መሰል ላልተሰራባቸው እንዲሁም ምንም አይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሳይኖር ከ210 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክን አድርገዋል፡፡

በሦተኛና በአራተኛ ክስ ደግሞ ከዱቬንቱስ ዊንድ ኩባንያ ጋረ በተያያዘ ግለሰቦቹ የኩባንያውን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው የባንክ እዳ ጭምር በመክፈል ከ149 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል በዋና ወንጀል አድራጊነት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ዛሬ በተነበበው ክስም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ባሉት ክሶች እስካሁን ያልተያዙና በቀጣይ የሚያዙ ወንጀለኞችን ጨምሮ አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛና በሦስተኛ ክሶች ደግሞ የዱቬንቱስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ዳንኤል ይግዛው ተካተውበታል፡፡

ክሳቸውን ያቀረበው የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሲሆን በቀረበው ክስ ላይ ብይን ለመስጠትና በፁሁፍ ያቀረቡትን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመመርመር ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡