ወጣቱ መጤና ጎጂ ልማዶችን እንዲታገል ተጠየቀ

90

ሐረር ሚያዝያ 13 / 2011 ወጣቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን እየጎዳ የሚገኘውን መጤና ጎጂ ልማዶችን እንዲታገል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አሳሰቡ።

በባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መስክ ለተሰማሩ ወጣቶች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በድሬዳዋ እየተሰጠ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሐብታሙ ሲሳይ በዚሁ ወቅት እንዳስገነዘቡት ወጣቱ በአገሪቱ እየተስፋፋ የሚገኙ አጓጉል ሱሶች ፣ ከውጭ የሚገቡ ጎጂ የሥነጥበብና ኅትመት ውጤቶች  ራሱን መጠበቅ አለበት።

መጤና ጎጂ ባህል ወጣቱ በስፖርት እንቅስቃሴ አካልን ከማዳበርና ጤንነትን ከመጠበቅ ይልቅ በሱስ ተጠምዶ ጤናው እንዲታወክ፣ የሥራ ተነሳሽነትእንዲያጣና በረብሻና ሁከት እንዲሳተፍ መንገድ እየከፈተ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህም የአገሪቱን ማህበራዊና ባህላዊ ትስስሮች እንዲላሉና እንዲሸረሸሩ፣ጠቃሚና ባህላዊ እሴቶች እንዲዳከሙና የእምነትና የኃይማኖትሥርዓቶች እንዳይከበሩ እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ባህላዊ የመደጋገፍና የመረዳዳት ልምዶች በግለኝነት አስተሳሰብ ምክንያት ለአደጋ  መጋለጣቸውን  ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር መድረኩ ወጣቱ ልምዶችና ተሞክሮዎች የሚለዋወጥበት ፣ባህልና ወጉን የሚያስፋፋበት ፣ ባህላዊ የእርቅ አፈታት ልምድን የሚቀስምበትና መጤና ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት ለሌሎች ትምህርት የሚካፈልበት ነው  ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፈደሬሽን ተወካይ ወጣት በአምላክ ታደሰ በበኩሉ መድረኩ ወጣቱ የምክንያታዊ አስተሳሰብ ባለቤት እንዲሆንና በሥነ ምግባር የበለፀጉ ወጣቶችን ለማፍራት ይረዳል ብሏል፡፡

በተለይ በአገሪቱ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ የሚገኘው መጤና ጎጂ ልማዶችን በመከላከል ጠቃሚ ማህበራዊ እሴቶችን ለመገንባት እንደሚያነሳሳ ገልጿል፡፡፡

 ''የስብዕና ልማት ለመልካምነት! በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ መስተዳድር የተውጣጡ 170 ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

ለአራት ቀናት እየተካሄደ ባለው መድረክ ቆይታ  በፊልምና ባህል ፖሊሲ ፣ ወጣቶች ለስፖርት ዘርፍ ባላቸው ሚና፣ በባህል ትስስርና በሰላም ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም