በሰቆጣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቦታ አሰጣጥ ግልጽነትና ፍትሃዊነት ይጎድለዋል

68


ሰቆጣ ሚያዝያ 13 /2011 በሰቆጣ ከተማ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማህበራት ቦታ አሰጣ­ጥ የግልጽነትና ፍትሃዊነት ጉድለት እንደሚታይበት ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ በማህበራት ለተደራጁ ነዋሪዎች ቦታ የሚሰጥበት ሥርዓት ግልጽነትና ፍትሃዊነት ባማከለ መንገድ እየተከናወነ አይደለም።

ከነዋሪዎቹ መምህር ዓለማየሁ በየነ ከ2009 ጀምረው በቤት ሥራ ኅብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው የቤት ባለቤት ለመሆን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ገቢያቸውን መሠረት በማድረግም በየወሩ በመቆጠብ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ማሟላት እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በከተማው የኅብረት ሥራ ማህበራትን አመሰራረት ቅደም ተከተልን መሠረት ያደረገ የቦታ አሰጣጥ ሥርዓት ባለመተግበሩ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በማህበራቸው አመሰራረት ቅደም ተከተል ዕውቅና እንዲሰጥ ያቀረቡት ቅሬታም ምላሽ ባለማግኘቱ  ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት ተጣርተው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲሉም መምህር ዓለማየሁ ጠይቀዋል፡፡

መምህር ዓለማየሁ በየነ  ከመስከረም 2009 ጀምረው ምስራቅ የተሰኘ የመምህራን ቤት ሥራ ኅብረት ሥራ ማህበር መደራጀታቸውን ያወሳሉ፡፡

‘’የምናገኘውን ገቢ መሰረት በማድረግ በየወሩ እየቆጠብን እያንዳንዱ የማህበር አባል የሚጠበቅብንን የቁጠባ መጠን ማሟላት ችለናል‘’ ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በከተማው ኅብረት ሥራ ማህበራት በተመሰረቱበት ቀንን መሠረት አድርጎ እውቅና እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ማህበራቱ ለሚያደራጀው መሥሪያ ቤት ባመለከቱበት ጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት የከተማው አስተዳደር ፍትህና ዐቃቤ ሕግ የውሳኔ ሐሳቡን አስቀምጧል ያሉት መምህር ዓለማየሁ፣ የከተማው ከንቲባም በመጣው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት እንዲፈጸም ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን አስረድተዋል፡፡

በውሳኔው  መሠረት ተግባራዊ ሳይደረግ ግልጽነትና ፍትሃዊነት በጎደለው መንገድ በ2010ና በዚህ ዓመት ለተደራጁ ማህበራት ቦታ መሰጠቱ ቅሬታ ፈጥሮብኛል ይላሉ፡፡

አቶ አዳነ ቸኮለ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው እንዳሉት የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ከመስከረም 2009 አንስቶ ተደራጅተው ቁጠባ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ’’ እውቅና ባገኛችሁበት ቀን መሠረት ቦታ ይሰጣል’’  የሚለው ውሳኔ  ያለመፈጸሙ ቅሬታን እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

‘’ከሁለት ዓመት በፊት ቀድመን የተመሰረትን ማህበራት እያለን ግልጽነት በጎደለው መንገድ ባለፈው ዓመት የተደራጁ ማህበራት ቦታ እንዲያገኙ ተደርገዋል’’ ብለዋል፡፡

ይህም በተመሰረትንበት ቀን መሠረት ሳይደረግ የእውቅና አሰጣጡ አድሏዊ በሆነ መንገድ የተሰራ ነው ያሉት አቶ አዳነ፣ ግልጽነት ባለው መንገድ ባለመሰራቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በእኩልነት ተጠቃሚ እንዳላደረጋቸው አመልክተዋል፡፡

ወይዘሮ የሺ ፀሐዬ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ''ከመስከረም 6/2009 ጀምረን በቤት ሥራ ማህበር ብንደራጅም፤ የተመሰረትንበትን ቀን መሠረት ያደረገ የእውቅና አሰጣጥ ሥርዓት ባለመኖሩ ከእኛ በኋላ የተደራጁ ማህበራት የቦታ ተጠቃሚ ሆነዋል’’ ብለዋል፡፡

ግልፅነት የጎደለው አሰራር በመተግበሩ የሚመለከታቸው የሕግ አካላት መፍትሄ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡

የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት መንግሥቴ በበኩላቸው በከተማው ከ2008 ጀምሮ ከ3 ሺህ 500 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በ160 ማህበራት ተደራጅተው እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

ማህበራቱ እውቅና በተሰጠባቸው ቀን ጀምሮ ቅደም ተከተላቸውን መሠረት ተደርጎ የመሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ በመወሰኑ ቦታ የሚሰጣቸውን ማህበራት መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በቦታ አሰጣጥ ላይ ያነሳው ቅሬታም ኦዲት እንደሚደረግና በኦዲቱ መሠረት ችግር የፈጠሩ ባለሙያዎች በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በከተማው ሚጠበቅባቸውን መስፈርት ያሟሉ የቤት ሥራ ማህበራት ሕግና አሰራርን ተከትሎ ለ16 ማህበራት ለቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል ያሉት ደግሞ የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ በኃይሉ መኮንን ናቸው፡፡

በዚህም ከ320 በላይ የሚሆኑ አመልካቾች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከ130 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መምህራን እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሰቆጣ በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተች የሚነገርላት ከተማ ናት።

ከተማዋ በአሁኑ ወቅት  በሁለት የከተማ በሁለት የገጠር ቀበሌዎች የተዋቅረች ስትሆን፤ከ39 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሏት መረጃዎች ያመዐክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም