የመንገድ ተደራሽነትና ጥራት የመንገድ ደህንነት ሊሆን አይችልም- የትራንስፖርት ባለስልጣን

91

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2011 የመንገድ ተደራሽነትና ጥራት የመንገድ ደህንነትን ሊያረጋግጥ ስለማይችል መንገዶች ሲገነቡ ደህንነት ላይም ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የትራንስፖርት ባለስልጣን ገለፀ። 

የሚገነቡ መንገዶች ለመንገድ ደህንነት ትኩረትአለመስጠታቸው ለትራፊክ አደጋ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ነው ባለስልጣኑ ያስረዳው።

ባለስልጣኑ መንገዶችን ተደራሽ ለማድረግ እና ጥራትን ጠብቆ በሚሰራው ልክ በመንገድ ደህንነት ላይ በመስራት በተለይ በእግረኞች ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ መስራት እንዳለበት ነው የተናገረው።

ከ2006 እስከ 2009ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ከሞቱ ሰዎች መካከል 39 በመቶ ያህሉ እግረኞች ሲሆኑ 45 በመቶ ተሳፋሪዎች እንዲሁም ከ15 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ አሽከርካሪዎች መሆናቸው ያለው መረጃ ያሳያል።

በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዩሃንስ ለማ እንዳሉት በሀገሪቷ የመንገድ ተደራሽነትን ሽፋን ለማሳደግ በተሰራው ልክ በመንገድ ደህንነት ላይ አልተሰራም።

አብዛኛው ኀብረተሰብ እግረኛ በሆነባት ሀገር ተሽከርካሪን እንጂ እግረኛን ታሳቢ ያላደረገ መንገድ መገንባቱ የትራፊክ አደጋን ስለሚያባብስ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ ሊሰራ እንደሚገባ በማውሳት።

የመንገዶችን ግንባታ ከንድፈ ሃሳብ ጀምሮ እንዲሁም ከተገነቡ በኃላ አደጋ የሚበዛባቸውን መንገዶች እየለየ የመንገድ ደህንነት ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚከውን ኮሚቴ ማቋቋም እንደሚገባም አቶ ዮሃንስ አብራርተዋል።

ስለዚህ እግረኛን ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ምልክቶችና ማመላከቻዎች የተተከሉባቸው ምቹ መንገዶችን በመገንባት የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ መኖሩን ገልጾ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የሚሰራ መሆኑን አስረድቷል።

በባለስልጣኑ የዲዛይን ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበልኝ መኩሪያ እንዳሉት ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት የገነባቸው መንገዶች አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥም በባለስልጣኑ የሚገኘው የመንገድ ሃብት ዳይሬክቶሬም አደጋ የሚበዛባቸውን ቦታዎች በመለየት መፍትሄ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ የሚሰሩ መንገዶች እግረኞችን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆን ለማስቻልም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ሰውን ማዕከል አድርገው መስራት አለባቸውም ብለዋል።

ባለስልጣኑ በቀጣይ የሚሰራቸው ምልክትና ማመላከቻዎች ኀብረተሰቡ ሊረዳው በሚችለው መልኩ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም