የኦሮሞና አማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው 

593

አምቦ ሚያዚያ 13/2011 የኦሮሞና አማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጉባኤ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

የዛሬ ሁለት ዓመት በቀድሞ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ሐሳብ  አመንጭነት የሁለቱ ክልሎች ህዝቦችን የበለጠ የማቀራረብ ጉዳይ በዚያኔው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተቀባይነት አግኝቶ የአማራና ኦሮሞ ግንኙነት ደምቆ የታየበት ጊዜ ነበር።

በወቅቱ የነበረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፍሬ አፍርቶም አሁን በአገሪቷ ላይ  እየታየ ላለው ለውጥ መሰረት ሆኗል።

የሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች የቆየ አብሮነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠልም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ትናንት ነበር የህዝብ ልዑካን  ቡድኑን መርተው ወደ አምቦ ከተማ ያቀኑት።

ትናንት ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ልዑካን ቡድንም ዛሬ ከአምቦ ከተማና  አከባቢዋ ነዋሪዎች ጋር የህዝብ ለህዝብ ጉባዔ በማካሄድ ላይ ናቸው።

በዶክተር አምባቸው የተመራውን ልዑክ ደማቅ አቀባበል በማድረግ ትናንት  ማምሻውን የተጀመረው መድረኩ በኃይማኖት አባቶችና በአባ ገዳዎች ምርቃት ተከፍቷል።

የአምቦ ከተማ ከንቲባ ተረፈ በዳዳ የኦሮሞ ነፃነት ትግል ቀዳሚዋ ተሰላፊ ወደ  ሆነችው አምቦ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል መልክታቸው የአማራና ኦሮሞ ጥንታዊና ታሪካዊ አንድነትና አብሮነት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስለሆነም ለጥቅማቸው ሲሉ በህዝቦች መካከል መቃቃርና ጥርጣሬን  የሚፈጥሩትን በመታገል ሁለቱ ህዝቦች የነበራቸውን ታሪካዊ ግንኙነት መመለስ ይገባል ብለዋል።

ዛሬ እንግዶቹን በፈረሰኞች በማጀብ የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ጉባኤው  በአምቦ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ሲሆን አሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሰክሬተሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁንና የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም ታድመውበታል።

‘ኦሮሞ የኛ፣አማራ ኬኛ፣ ሁለቱም የኛ’ የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።