የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

81

ሚያዝያ 12/2011 የግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ግብርና እስካሁን በነበረው አሰራር ከቀጠለ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት አዳጋች ይሆናል አለ።

በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ አስካሁን በሄደበት መንገድ እንዳይቀጥል ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ የምሁራንና የግብርና ባለሙያዎች ሚና ለግብርና ትራንስፎርሜሽን’በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

የኢትዮያን ግብርና በተለያዩ ጊዜያት ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተወሰዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችና እርምጃዎች የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣታቸው ተነስቷል።

ለዚህ ደግሞ ዘርፉ የዝናብ ጥገኛ መሆኑ፣ የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ ለዘርፉ የተሰጠው የተዛባ አመለካከት በዋናነት ተጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ዘርፉ አስካሁን በሄደበት አሰራር ከቀጠለ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አዳጋች በመሆኑ በተለይ ምሁራን ከፖሊሲ ጀምሮ አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አብዛኞቹ ምርቶች ለገበያ ተብለው በዕውቀት ላይ ያልተመሰረቱና በትናንሽ እርሻዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ናቸውም ብለዋል።

በሰብልና በእንሰሳት ሃብት ምርትና ምርታማነት ላይ ያሉ ችግሮች በአግባቡ በጥናት መለየቱን የገለጹት ሚኒስትሩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አንስተዋል።

ስንዴ ፣ቡና እና ዶሮ እርባታ በአጭር ጊዜ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲያድግ የተለየ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ለዚህም አስቻይ ሁኔታ መኖሩንና የውጭ ምንዛሬንም ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በስንዴ አምራችነቷ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃን የያዘቸው ኢትዮያ የመስኖ ልማትን በመጠቀም ምርታማነቷን ማሳደግ ከቻለች ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕድል እንዳላትም ጠቅሰዋል።

ለዚህም እኤአ በ2023 የስንዴ ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ በአገር ወስጥ ምርት ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን ለእቅዱ መሳካት ሁሉም የዘርፉ ተዋንያን የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ሚኒስቴሩ በረጅም ጊዜ የግብርና ፖሊሲውን ለመቀየር በአጭር ጊዜ ደግሞ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ላይ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት የተለያዩ የህግና የፖሊሲ ማሻሻያ ስራዎችን ለመሰራት ጥረት እያደረገ መሆኑም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የክልል አመራሮች ከሃብት አመዳደብ እስከ አመራር መስጠት ያላቸውን ድርሻ በአግባቡ እንዲያውቁት ማድረግና የዘርፉ ምሁራንም ዕውቀታቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅረበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት መደረግ የመፍትሄ ሀሳብ ያሏቸውንም ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችንና ተግዳሮቶችን አንስተው ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም