ኮሌጁ ያሰለጠናቸውን ከአንድ ሺህ 600 በላይ የአድማ ብታና ፖሊስ አባላትን አስመረቀ

104

ሚያዝያ 12/2011 የአማራ  ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በደበረማርቆስ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን ከአንድ ሺህ 600 በላይ የአድማ ብታና ፖሊስ አባላትን  ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃው ስነስርዓት የተገኙት የክልሉ የሰላም ግንባታና ደህንነት ቢሮ  ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ጽጌ እንደተናገሩት ፖሊስ የህዝብን አደራ ተሸክሞ ለሰላም ግንባታ ህይወቱን እስከ መስጠት ድረስ ዘብ የሚቆም ኃይል ነው።

ሳይንሳዊ ዕውቀትና ክህሎት የተላበሰ የፖሊስ ኃይልን በአቅም፣ በእውቀትና በክህሎት በማነፅ በክልሉ የህግ የበላይነት የማረጋገጥና  አስተማማኝ ሰላም የማስፈኑ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ኃላፊው እንዳመለከቱት ተመራቂ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላትም ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ ከነባር አባላት ጋር በመሆን ሳይሰለቹ ለመስራት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ህዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባና በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ ሌላኛው ተልኮአቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የአማራ ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር አብሮ የቆየውን ወንድማማችነት፣ መቻቸልና የመከባበር ባህል ለማፍረስ ጥረት የሚያደርጉ ህጉን መሰረት አድርገው ከዕኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በመስራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አንማው አለሜ በበኩላቸው ተቋሙ ሰላም እንዲሰፍንና መልካም አስተዳደር እንዲገነባ የፖሊስ አባላትን በየጊዜው እያሰለጠነ ወደስራ በማሰማራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢውን የጸጥታ ኃይል ለማሟላትም  ከአንድ ሺህ 600 በላይ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላትን ለአምስት ወራት ተኩል አሰልጥነው ዛሬ  ማስመረቃቸውን  ተናግረዋል።

በስልጠናው በንድፍ ሀሳብ እና በተግባር ሙያው የሚፈልገውን እውቀትና  ክህሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

ከሰለጠኑባቸው መስኮች ውስጥም የወንጀል መከላከል፣ የህገወጥ ሰልፍና አድማ ብተና እንዲሁም የፖሊስ ጥበብና አካል ብቃት ይገኙበታል።

ተመራቂዎቹ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ተመልምለው በማሰልጠኛ ኮሌጁ ገብተው የሰለጠኑ ናቸው " ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ ከመካከላቸም ከ200 በላይ ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ከደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ ጋይንት ወረዳ የመጣችው ኮንስታብል ላቄ አበረ በሰጠችው አስተያየት የፖሊስነት ሙያ ህዝብን ማገልገል በመሆኑ የጣለባትን  አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

በስልጠና ቆይታዋ ያገኘችውን እውቀት ግባር ላይ በማዋል ህዝቡን ከአደጋ ለመጠበቅ የዜግነት ድርሻዋን እንደምትወጣም ገልጻለች።

ስልጠናውን ወስዶ ለዛሬዋ የምርቃ ቀን መብቃቱ እንዳስተው የተናገረው ደግሞ ከባህርዳር ከተማ  ቀበሌ 11 የመጣው ኮንስታብል መልካሙ አለሙ ነው።

በቀጣይ በምመደብበት የስራ ቦታ የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅ ኃላፊነቴን ለመወጣት በቂ የአካልና የስነልቦና ዝግጅት አድርጌአለሁ" ብሏል።ቦና ዝግጅት አድርጌአለሁ" ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም