ኢትዮጵያ የቻን ውድድር አዘጋጅነቷን የተነጠቀቸው ለማስተናገድ ብቁ ባለመሆኗ ነው - የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን

71

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2020 የአፍሪካ አገራት የእገር ኳስ ውድድር (ቻን) አዘጋጅነቷን ኢትዮጵያ የተነጠቀችው ውድድሩን ለማስተናገድ ብቁ ባለመሆኗ እንደሆነ አስታወቀ።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያ የቻን አስተናጋጅነት መነጠቋን በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚገኘው የፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2017 በ2020 የሚዘጋጀውን ስድስተኛውን የአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱበትን የአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር (ቻንን) ለማዘጋጀት ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2018 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው አምስተኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የቻን ውድድር የአዘጋጅነት አርማ በይፋ መረከቧም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ የአስተናጋጅነቷ ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የዝግጅት ስራዎች እያደረገች ቆይታለች።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የቻን ውድድር አስተናጋጅነቷን ነጥቆ ለካሜሮን መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለቦች ፈቃድ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ተድላ ዳኛቸው እንዳሉት ካፍ የኢትዮጵያን አስተናጋጅነት የነጠቀው ውድድሩን የማስተናገድ ብቃት ስለሌላት እንደሆነ ተናግረዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የተቆጣጣሪ ቡድን ሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም እና መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መገምገሙን አስታውሰዋል።

በባለፈው ዓመት ጉብኝት የካፍ ባለሙያዎች አጠቃላይ ስድስት ስታዲየሞች፣12 የልምምድ ሜዳዎች፣20 ሆቴሎችና አምስት አየር ማረፊዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣የመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣የድሬዳዋ ስታዲየም፣የሐረሪ ስታዲየምና የአደይ አበባ ስታዲየምን ተመልክተዋቸዋል።

በመጀመሪያው ዙር ምልከታ የኦዲት ሪፖርት ከአደይ አበባ ስታዲየም በስተቀር ሌሎቹ ስታዲየሞች የቻን ውድድርን ለማዘጋጀት ካፍ ያወጣቸውን መስፈርቶች የማያሟላ መሆኑን መግለጻቸውን አመልክተዋል።

ስታዲየሞቹ የሚያስፈልጋቸውን በቂ መሰረተ ልማት አለማሟላት፣ የግንባታ ሁኔታቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያስረዳ ባለሙያ አለመኖሩና በተቀመጣላቸው ጊዜ ግንባታቸው እየተፋጠነ አለመሆኑን አንስተዋል።

ሁሉም የልምምድ ሜዳዎች ከሚያስፈልገው ደረጃ በታች እንደሆኑና በአየር ማረፊያና በሆቴሎች ዝግጅት ግን መርካታቸውን ጠቅሰዋል።

በሁለተኛውም ዙር የምልከታ ግምገማም በተሰጡ ምክረ ሀሳቦች ላይ የተደረጉ ጥሩ ማሻሻያዎች ቢኖሩም የስታዲየሞች ግንባታ መጓተት ችግር መቀጠሉንና በልምምድ ሜዳዎች ላይም ምንም አይነት ለውጥ እንዳላዩ የካፍ ባለሙያዎች መግለጻቸውን ነው ዶክተር ተድላ ያስረዱት።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን መስፈርቶች ባለማሟላቷ የአዘጋጅነት እድሉን መነጠቋን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን እንደማታዘጋጅ ለካፍ አሳውቃ ነው ካፍ አዘጋጅነቱን ለካሜሮን የሰጠው የሚባለው መረጃ ትክክል እንዳልሆነና የተነጠቅነው የማዘጋጀት አቅማችን ያነሰ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ከካፍ የስራ ሃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት ኢትዮጵያ ካፍ ያስቀመጠቸውን መስፈርቶች ካሟላች እ.አ.አ በ2022 የሚዘጋጀውን ሰባተኛውን የቻን ውድድር እንድታዘጋጅ ካፍ እድል እንደሚሰጣት ቃል መግባቱንም ጠቁመዋል።

በስታዲየሞች ግንባታ ላይ ያለው ጉዳይ አሁንም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነና ለዚህም ክልሎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የአዘጋጅነቱን ጥያቄ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ እንደቀረበ አስታውሰው ባለው ሁኔታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄ አለመቅረቡን አብራርተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ባይቀርብም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውድድሩን ለማስተናገድ 300 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉንና ሌሎች ጉዳዮችን ያካተተ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ቢቀርብም ሚኒስቴሩ ምላሽ እንዳልሰጠ አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ወድድሩ በቀጣይ ኢትዮጵያ የምታናስተናግድ ከሆነ መንግስት የነበረውን ቁርጠኝነት ማስቀጠልና ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አንደሚገባው አሳስበዋል።


በጥር ወር 2012 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚካሄደው ስድስተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር አስተናጋጇ አገርን ጨምሮ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ እ.አ.አ በ2018 የተካሄደውን የቻን ውድድር በመጀመሪያ ለኬንያ የማስተናገድ እድል ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ኬንያ ለውድድሩ ያደረገችው ዝግጅት ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ እድሉን ለሞሮኮ መስጠቱ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም