ለጽዳት የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው በስራቸው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው በመቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በፅዳት ስራ የተሰማሩ ሴቶች ተናገሩ

64

መቀሌ - ሚያዝያ 12/11ዓ/ም ለጽዳት የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው  በስራቸው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው በመቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በፅዳት ስራ የተሰማሩ ሴቶች ተናገሩ ።

የከተማው ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት  በበኩሉ ፣የሴቶቹ ችግር ለመፍታት የቁሳቁሶቹ ግዥ መፈጸሙንና በቅርቡ እንደሚታደላቸው ገልጿል።

በስራው ከተሰማሩ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ፉርትና ጉዕሽ እንዳሉት፣በጽዳት ወቅት የእጅ ጓንት፣ጫማና የአባራ መከላከያና ሌሎች ተጓዳኝ  ቁሳቁሶች ያስፈልጋቸዋል።


እነዚህ ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው ቆሻሻው በእጃቸው ለመጥረግ ስለሚገደዱ በእሾህና መሰል ስላታም ነገሮች በመጋለጥ እየተጎዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"የጠረግነው ቆሻሻ ለማጠረቀም ከራሳችን ካርቶን፣ አሮጌ ጆንያና ኬሻ ስለምንጠቀም በየመንገዱ እየተቀደደ ደረቅ ቆሻሻው በየቦታው ይደፋብናል" ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ብርሃን መብራቱ ናቸው።

ወይዘሮ ያለም አብርሃ በበኩላቸው፣በቁሳቁስ አለመሟላት የተደፋባቸውን ቆሻሻ እንደገና ለመሰብሰብ ተጨማሪ ድካምና የስራ ድግግሞሽ እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

"ያሉብንን ችግሮች ለከተማው ፅዳትና ውበት ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ቁሳቁሶቹ ይገዛሉ እየተባለ ከስድስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል" ብለዋል።

የከተማው ፅዳትና ውበት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ሞጎስ ፋንታዬ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የሴቶቹ ችግር በወቅቱ ለመፍታት ያልተቻለው በግዥ መጓተት ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

"አሁን ለስራው የሚያስፈልጉ የስራ ቁሳቁሶች በመገዛታቸው ችግሩ ይቃለላል" ብለዋል።

የተገዙትን ቦቴ ጫማ ፣ ቆብ፣ የእጅ ጓንት፣ ሽርጥና ሌሎች ቁሳቁሶች በቅርቡ በነፍስ ወከፍ ለሰራተኞቹ እንደሚከፋፈላቸው አስረድተዋል።

"በተጨማሪም ቆሻሻ ለማንሳት አገልግሎት የሚውሉ አካፋ፣ መጥረጊያ፣ ዶማ፣በእጅ የሚገፉ ጋሪዎች እንደሚሰጣቸውናየመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ኪትም ይታደላቸዋል "ብለዋል።

በከተማው ሦስት ሺህ 244 ሴቶች ተደራጅተው በከተማው ፅዳት ስራ ተሰማርተው እንደሚገኙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም