ጤፍን በመስኖ ያለሙ አርሶ አደሮች በሄክታር 28 ኩንታል ምርት አገኙ

290

ሚያዝያ 12/2011በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ጤፍን በመስኖ ያለሙ አርሶ አደሮች በሄክታር 28 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገለጹ፡፡

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ የጤፍ መስኖ ልማቱ በመኸር እርሻ ከሚገኘው የጤፍ ምርት በሄክታር የሦስት ኩንታል ምርት ጭማሪ እንዳለው አስታውቋል፡፡

አርሶ አደር ጌትነት ሰንደቅ በወረዳው የአባዋርካ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ጤፍን በመስኖ አልምተው ከግማሽ ሄክታር 14 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

” ጤፍን በክረምትም ሆነ በበጋው ማልማት እንደሚቻል በተግባር አረጋግጫለሁ ” ያሉት አርሶ አደር ጌትነት በዓመት ሁለት ጊዜ ጤፍን የማልማቱን ሥራ ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል፡፡

በበጋ ጤፍን በመስኖ ማልማት ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ደግሞ በወረዳው የምጥርሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጥላሁን አሰፋ ናቸው፡፡

የበጋ የጤፍ መስኖ ልማት ከዝናብ መብዛት፣ ከበረዶ፣ ከጎርፍና ከዋግ በሽታ ነጻ በመሆኑ የምርት መቀነስ ያጋጥማል የሚል ስጋት እንዳላደረባቸው ጠቅሰዋል፡፡

አርሶ አደር ይበልጣል ካሴ በበኩላቸው በ90 ቀናት ውስጥ የሚደርሰውን ቁንጮ የተባለውን የጤፍ ዝርያ በሩብ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ በመስኖ ማልማታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሰብሉ ለአጨዳ በመድረሱ እየሰበሰቡ መሆኑንና ከመስኖ ልማቱም 7 ኩንታል የጤፍ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

በመስኖ ልማቱ የተሰማሩት አርሶ አደሮች ለውሃ ማጠጫ በስፋት የሚጠቀሙበት የውሃ መሳቢያ ሞተር አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ጠቁመው በቀጣይ ችግሩ እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል፡፡

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባይለየኝ አድማሱ በበኩላቸው “በዘንድሮ የበጋ ወራት 120 አርሶ አደሮች በ40 ሄከታር መሬት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጤፍን በመስኖ እንዲያለሙ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በመኽር እርሻ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 25 ኩንታል ጤፍ በመስኖ ልማቱ ወደ 28 ኩንታል በማሳደግ አርሶ አደሩ የ3 ኩንታል የምርት ጭማሪ አግኝቷል፡፡

በመስኖ የሚለማው ጤፍ በክረምት ወቅት ከሚያጋጥመው ጎርፍ፣ በረዶና የዝናብ መብዛት የተፈጥሮ አደጋ ነጻ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ በቀጣዩ ዓመት በመስኖ የሚለማውን የጤፍ መሬት ወደ 2ሺህ ሄክታር በማስፋት የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቁጥር ወደ 500 ለማሳደግ ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡         

“የመስኖ ውሃ አጠጣጥ ቴክኖሎጂን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ባለሙያዎች እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

በወረዳው በዘንድሮ የበጋ ወራት 12ሺህ 422 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና የሰብል ምርት የተገኘ ሲሆን በመስኖ ልማቱም 33ሺህ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡