በቻይና እና ጃፓን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል ይጠበቃሉ

64

ሚያዝያ 12/2011 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በቻይና እና በጃፓን በሚካሄዱ ዓለም  አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝተዋል።

በቻይና የየሎው ሪቨር ኢስቱዋሪ ዓለም አቀፍ ማራቶን  በሴቶች አትሌት ዋጋነሽ መካሻ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት አግኝታለች።

አትሌት ዋጋነሽ በጥር ወር 2011 ዓ.ም በተካሄደው የዱባይ ማራቶን 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን አስመዝግባለች።

በመሆኑም በነገው ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል የተሻለ ሰአት እንዳላትም የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

   አትሌት አፈራ ጎድፋይ በውድድሩ የምትሳተፍ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ናት።

 በወንዶች አትሌት ግርማይ ብርሃኑ እና አትሌት ፍቃዱ ከበደ የሚሳተፉ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች ብርቱ ፋክክር ያደርጋሉ ተብሎ  ይጠበቃል።

 ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው የየሎው ሪቨር ኢስቱዋሪ ዓለም አቀፍ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

 በጃፓን በሚካሄደው የናጋኖ ማራቶን ውድድርም በወንዶች አትሌት ደጀኔ ከልክለው እና አትሌት ደሬሳ ገለታ  ይሳተፋሉ።

 በሴቶች አትሌት ትዝታ ተሬቻ፣ አትሌት መስከረም ሁንዴና አትሌት ቀበኔ ጫላ የሚሳተፉ ይሆናል።

 በናጋኖ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች የኬንያ አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል።

 ለ21ኛ ጊዜ የሚካሄደው የናጋኖ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

 በተጨማሪም ነገ በቻይና በሚካሄደው የያንግዙ ጂያንዜን ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት  አግኝታለች።

 ባለፈው ዓመት በጣልያን በተካሄደው የሚላኖ የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ሱቱሜ 1 ሰአት ከ7 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን  ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አትሌት ደጂቱ አዝመራው የአትሌት ሱቱሜ ዋንኛ ተፎካካሪ መሆኗን የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል።

 በወንዶች አትሌት ብርሃኑ ፅጉ የሚሳተፍ ሲሆን ኬንያውያን አትሌቶችም በውድድሩ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ተገምቷል።

 በባለፈው ዓመት የያንግዙ ጂያንዜን ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን በሴቶች አትሌት አባብል የሻነህና በወንዶች አትሌት ሞስነት ገረመው ማሸነፋቸው የሚታወስ  ነው።

ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄደው  የያንግዙ ጂያንዜን ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም