የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ሀብት ለማፍራት እንደጠቀማቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ

247


ቀምቴነገሌ ሚያዝያ 12/2011 ዓ.ም  በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ  መሰማራታቸው  ሀብት መፍጠር ማስቻሉን  በሆሮ  ጉዱሩ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ የምርጥ ዘር እጥረትና የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ለበልግ አዝመራ ስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው በጉጂ ዞን የሊበን ወረዳ አርሶ አደሮች አመልክተዋል።

በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ሆሮ ወረዳ የግትሎ ደሌ ቀበሌ በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ  ከተሰማሩት መካከል አርሶ አደር ደበሎ ዲባ የምርጥ ዘር ብዜቱን 46 ሆነው በ2006 ዓ.ም መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት በቡድን ተደራጅተው በምርጥ ዘር ብዜት ስራ ላይ መሰማራታቸው ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።

በ2010/2011 የምርት ዘመን 40 ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘር  አምርተው ለሽያጭ በማቅረብ ያገኙት ከ57 ሺህ  ብር በላይ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያልነባራቸውን የእርሻ በሬ ባለቤት መሆን እንዳስቻለው የገለጹት አርሶ አደሩ የውስጥ ገቢያቸው በማደጉ በኑሯቸው መለወጣቸውን አመልክተዋል።

መኖሪያ ቤታቸውን ከሣር ወደ ቆርቆሮ ከመለወጥ አልፈው በከተማ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት መገንባታቸውንም  አስረድተዋል።

በዚሁ  ወረዳ የለኩ እጉ ቀበሌ  አርሶ አደር አሰበ ጋሮማ በበኩላቸው በምርጥ ዘር ብዜት ስራ በመሰማራታቸው ኑሮቸውን ለመለውጥ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም በግላቸው 90 ኩንታል የምርጥ ዘር ብዜት በማምረት በዞኑ ለሚገኘው የጨፌ ቡሉቅ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ዩኒዬን በመሸት 128 ሺህ 700 ብር ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ከምርጥ ዘር ብዜት ስራ ባገኙት ገቢ 70 ሺህ ብር በባንክ እንደቆጠቡ አመልክተው የእህል ወፍጮና የባጃጆች ባለቤት መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።

በማህበር ተደራጅተው በ60 ሄክታር መሬት ላይ ከሚያለሙት ምርጥ የበቆሎ ዘር በተያዘው  ዓመት ብቻ 1 ሺህ 447 ኩንታል ካገኙት በተጨማሪ በግላቸው 42 ኩንታል አምርተው በመሸጥ 45 ሺህ 570 ብር ገቢ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በአሙሩ ወረዳ የሐሮ ጉዲና ቀበሌ አርሶ አደር በቀለ ዱፌራም ናቸው።

የወረዳው የአገምሣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መርጋ ጀምበሬ   እንዳሉት ወደ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ ከጀመሩ ሁለት ዓመታቸው ሆኗቸዋል።

በ2010/2011 የምርት ዘመን 63 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር አምርተው በመሸጥ 69 ሺህ 300 ብር ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

የጨፌ ቡሉቅ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ነመራ ዩኒዬኑ አርሶ አደሮቹ የሚያባዙትን ምርጥ ዘር በተመጣጣኝ ዋጋ እየተረከበ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በጅማ ገነቲ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች በማህበር እንዲደራጁ በማድረግ በተያዘው ዓመት ወደ ምርጥ ዘር ብዜት እንዲገቡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያያዘም የምርጥ ዘር እጥረትና የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር በበልግ አዝመራ ስራቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው ያመለከቱት ደግሞ በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ናቸው።

ከወረዳው ለጋጉላ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ  ተሬ ጉዮ ባለፈው ዓመት ኩንታሉን  ማዳበሪያ በ1 ሺ 240 ብር መግዛታቸውን አስታውሰዋል፡፡ዘንድሮ ካለፈው 484 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመው ለበልግ አዝመራ ያዘጋጁትን ሶስት ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፈን የምርጥ ዘር እጥረትና የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ተዳምሮ  እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የመሊሶ ቀበሌ አርሶ አደር  ሀለኬ ጎዳና በበኩላቸው ሁለት ሄክታር መሬት በጤፍ ዘር ለመሸፈን የሚያስፈልጋቸውን ሁለት ኩንታል ምርጥ ዘር ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ለበልግ አዝመራ ካዘጋጁት  አራት ሄክታር መሬት ሁለት ሄክታሩን በጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ያስረዱት ሌላው አርሶ አደር ሊበን ጉራቻ በምርጥ ዘር ችግር የአዝመራ ወቅት እያለፈባቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት በጉጂ ዞን የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የምርት ግብአት አቅርቦት ባለሙያ አቶ ደምሴ ሀሮ  በሰጡት ምላሽ በማዳበረያ ጥራት መሻሻልና በውጭ ምንዛሪ ጭማሬ ምክንያት መጠነኛ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉን  ገልጸዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን የገለጹት ባለሙያው የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለማቃለል ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት 5 ሺህ 695 ኩንታል ምርጥ ዘርና 40 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪ መቅረቡን አስረድተዋል።