ህጋዊ የዋጋ ጣሪያና የዋጋ ወለል አለመኖሩ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል - የምጣኔ ሃብት ባለሙያ

64

ሚያዝያ 12/2011 በኢትዮጵያ ህጋዊ የዋጋ ጣሪያና ህጋዊ የዋጋ ወለል ባለመኖሩ በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ይናገራሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ሸዋአፈራሁ ሽታሁን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት “ሸማቹ ህጋዊ  የዋጋ ጣሪያ፤ አምራቹ ህጋዊ የዋጋ ወለል እንዲኖር መንግስትን የሚጠይቅበት ስርዓት አለመኖሩ በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዋጋ እንዳይኖር አድርጓል”።

በዚህም ምክንያት የዋጋ ንረቱ ያለማቋረጥ እንዲጨምር ከማደረጉም ባለፈ ሸማቹ ለአላስፈላጊ  ወጭ እየተዳረገ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የግብይት ሰንሰለቱ አለመዘመን አቅራቢው ላይ ተገቢው ቁጥጥር እንዳይደረግ አድርጓል ያሉት ባለሙያው፤ አንድ ምርት በምን ያህል ዋጋ ተመርቶና ተጓጉዞ ተጠቃሚው ጋር ይደርሳል የሚለውን ለመወሰን አስቸጋሪ በመሆኑ ነጋዴው እንደፈለገ ዋጋ እንዲጨምር እድል ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

 “ገበያ-መር ኢኮኖሚለኢትዮጵያ ቅንጦት ይመስለኛል” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ባልዳበረ ሀገር ብቻ ሳይሆን ባደጉ ሀገራትም መንግስት የኢኮኖሚ ቀውስ ሲከሰት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የማረጋጋት  ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በአቅም ማነስ የግል ባለሃብቱ ሊገባባቸው በማይችልባቸው ዘርፎች መንግስት ሚናውን በመወጣት የግል ዘርፉን እያስከተለ መንገድ ማሳየት ይኖርበታል የሚሉት አቶ ሸዋአፈራሁ፤  በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ በሸማቹ ላይ የሚያርፈውን ጫና ለመቀነስ የመንግስት ጣልቃ መግባት  ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ሸማቹ የገበያ የዋጋን በመውሰድ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም፤ ሻጩ ያለ በቂ ምክንያት ዋጋ ሲጨምር አልገዛም ብሎ ተጽእኖ ከማሳደር ይልቅ በተጠየቀው ዋጋ ስለሚገዛ ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት የመንግሰት ስርዓቶች ጭምር ኢኮኖሚው ላይ በሚደረገው ፖለቲካዊ ጫና ሁሉንም አካታች ባለመሆኑ ኢኮኖሚው ለስርአቱ ቅርበት ላላቸው በጥቂት ባለሃብቶች እጅ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ  በሂደት ባለሃብቶች እራሳቸው መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር ኢኮኖሚውን እንደ ፈለጋቸው እንዲያደርጉ እድል ይሰጣል ይላሉ፡፡

በንግድ ስራ ዘርፍ  የተሰማሩ አስተያየት ሰጭዎች  በበኩላቸው  የዋጋ  ጭማሪ የሚያደርጉት ተገቢ ያልሆ ትርፍ ለማግኘት  ሳይሆን በገያው አስገዳጅ  ሁኔታዎች  መሆኑን  ይናገራሉ፡፡

በየጊዜው የሚጨምረው የመስሪያ ቦታ ኪራይ፣ ግብርና ተያያዥ ወጭዎችን ለመሸፈን የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እንገደዳለን ያሉት የፍጆታ ምርቶች ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ሃይሉ ብርሃኑ ናቸው።

እንደ ጊዜውና እንደወቅቱ ዋጋ ካልጨመርን ስራውን ከማቆም በስተቀር አዋጭነት አይኖረውም በማለትም ይገልጻሉ።   

“ባለው ነባራዊ የገበያ ሁኔታም ቢሆን በደንበኞች ላይ ዋጋ መጨመር ከማሳቀቁም ባለፈ ደንበኞችን ያሸሽብኛል” የሚል ስጋት እንደሚያሳድርባቸው የሚናገሩት ደግሞ በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ሙስጠፋ ናሲ ናቸው፡፡

“እዚህ ሻጭ ብሆንም ሌላ ቦታ ገዥ ነኝ” ያሉት አቶ ሙስጠፋ የዋጋ ጭማሪው በተዘዋዋሪም ቢሆን በሁሉም ሰው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

ገቢ ሳይጨምር ማቆሚያ የሌለውን የዋጋ ጭማሪ ጫናን ተቋቁሞ ህወይትን መምራት ፈታኝ ነው ያለችው በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥራ በምታገኘው ገቢ ህወቷን የምትመራው ህይወት በቃሉ፤ የምርቶች ዋጋ መጨመር እንጂ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት መቀነስ አይታይም ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም