በአክሱም ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ከተካሄደባቸው 250 ፕሮጀክቶች መካከል ጥቅም ላይ የዋሉት 10 ፕሮጀክቶች መሆናቸው ተገለጸ

136

አክሱም ሚያዝያ 11/2011 በአክሱም ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ከተካሄደባቸው 250 ፕሮጀክቶች መካከል ጥቅም ላይ የዋሉት 10 ፕሮጀክቶች መሆናቸውን የዩኒቨርስቲው ጥናትና ምርምር አስታወቀ።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዩኒቨርስቲው ስምንተኛ ዙር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቅቋል። 

የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ንጉስ ገብረ ጊዮርጊስ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከ2005 ጀምሮ ከተካሄዱት ችግር  ፈቺ  ጥናቶችና የምርምር ውጤቶች እስካሁን ወደ  ህብረተሰቡ ወርደው ተግባር ላይ የዋሉት 10 የምርምር ፕሮጀክቶች ብቻ ናቸው።

በዩኒቨርስቲው የተሰሩትየምርምርና ጥናት ውጤቶች ወደ ታች ወርደው ተጠቃሚውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያላደረጉት  ተመራማሪዎች  በየደረጃው  ከሚገኙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው ባለመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ምሁራንና ፖሊሲ አውጪዎች በየደረጃው ካሉት የመንግስት አመራር አካላት ተቀራርበው ውጤቶቹ ተገምግመው ጥቅም የሚውልበት አቅጣጫ ያለመኖሩንም አስረድተዋል።

የምርምር ውጤቶቹ ወደ ታች ወርደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከመንግሥት አወቃቀር ጋር የሚስማሙ አሰራሮችን በመቅረጽ   ተግባራዊ  እንዲሆኑ  ከስምምነት መደረሱን አስረድተዋል።

የመቀሌ  ዩኒቨርሲቲ መምህርና ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ ምሁራን በጥናትና ምርምር እውቀታቸውን በማዳበር ለአገር ልማት እንዲያውሉት አሳስበዋል።

'የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻልና ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን አስተዋጽኦ  ከፍተኛ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ምትኩ፣ ምሁራን  ችግር  ከመናገር  ባለፈ   የችግሮች  መፍትሄ  ማሳየት  እንዳለባቸው  ገልጸዋል።

የምርምር ውጤቶች ወደ ኅብረተሰቡ ወርደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ተወካይ  አቶ ገብረ ሚካኤል  ተስፋይ  በከፍተኛ  የትምህርት  ተቋማት  የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ችግር ፈቺነት በጥልቀትና  በዝርዝር  ሊታይ  ይገባል ብለዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ 40 ያህል የጥናታዊና የምርምር ጽሑፎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጨምሮ በትግራይ ክልል ከ20 በላይ መንግሥታዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም