የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከኳታር ወደ አገሯ የተመለሰችውን ሜሮን መኮንን ጠየቁ

220

ሚያዝያ 11/2011የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ትናንት ወይዘሮ ሜሮንን  መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከወይዘሮ ሂሩት ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል፣ የዳያስፖራ እና ቆንስላ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ ዶክር ቦጋለ ቶሎሳ እና የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ጎፌ በሆስፒታሉ ተገኝተው ወይዘሮ ሜሮን ያለችበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

ወይዘሮ ሜሮን በኳታር በደረሰባት የከሰልጭስ መታፈን አደጋ ጉዳት ሳቢያ ላለፉት ስምንት ዓመታት በሀማድ ሆስፒታል በህክምና ላይ ቆይታ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን ወደ አገሯ መመለሷ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩትበወቅቱ ታማሚዋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄ ወደ አገሯ መመለስ በመቻሏ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ ዜጎች በአገራቸው እንዲታከሙ ማስቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ከሚሰሩ የውጭ አገሮች “የህክምና ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጥር ሚኒስቴሩ ይሰራል” ብለዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ታምሩ አሰፋ እንደተናገሩት፤ ወይዘሮ ሜሮን በተሻለ ጤንነት ላይ ትገኛለች። ሆስፒታሉም አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል።

የወይዘሮ ሜሮን መኮንን አስታማሚና ልጅ ቢኒያም ይልማ ለእናቱ ለተደረገላት ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች እንዲሁም በአገሪቷ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ እንዲሁም የኳታር መንግስትን አመስግኗል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እስካሁን ያሳየውን ወገንተኝነት እንዲቀጥል ጠይቋል።

የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰጣቸውን የማዋለድ፣ የልብ ቀዶ ህክምና፣ የድንገተኛ ህክምና፣ የተላላፊ በሽታዎች ህክምና እና ሌሎች ማዕከላት ላይ ጉብኝት ማድረጋቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኳታር መንግስት የወይዘሮ ሜሮን መኮንን ወደ አዲስ አበባ የመጣችበትን ሙሉ የትራንስፖርት ወጪ የሸፈነ ሲሆን፤ በአገር ቤትም ለአንድ አመት መታከሚያ የሚሆናትን ወጪ የሚሸፍን ይሆናል።