በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር የሁለተኛ ቀን ውሎ የተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተደርገዋል

138

አዲስ አበባ ሚያዝያ  11/2011 በደሴ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሶስተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር የተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተደርገዋል

ሚያዝያ 9 /2011 ዓ.ም በተጀመረው ውድድር በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተወጣጡ 63 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የሚደረግባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

ትናንት በውድድሩ የሁለተኛ ቀን ውሎ በወንዶች በ52፣54፣64፣69፣75፣81 እና 91 ኪሎ ግራም እንዲሁም በሴቶች 54 ኪሎ ግራም የማጣሪያ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

በ52 ኪሎ ግራም የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተወዳዳሪ ያዕቆብ በለጠ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚውን እዮብ አሰፋን በነጥብ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በ52 ኪሎ ግራም የድሬዳዋ ከነማው ኖኬ መሐመድ የደሴ ከነማውን ተወዳዳሪ አህመድ ይማምን በነጥብ አሸንፏል።

በ52 ኪሎ ግራም በተደረገ ሌላ የማጣሪያ ጨዋታ የማራቶን ክለቡን ተወዳዳሪ አዳነ አሳ የአዲስ አበባ ፖሊሱ ይድነቃቸው አቡሌን በነጥብ ረቷል።

በ64 ኪሎ ግራም የማራቶን ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው ጸጋዬ ተስፋዬ የድሬዳዋ ከነማውን ተወዳዳሪ እዮብ ነጋሽ በነጥብ አሸንፏል።

በ69 ኪሎ ግራም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተወዳዳሪው ሲራጅ ሙሉጌታ የድሬዳዋ ከነማውን ተወዳዳሪ ቢኒያም ተስፋዬ በዝረራ ሲያሸነፍ በተመሳሳይ በ69 ኪሎ ግራም የአዲስ አበባ ፖሊሱ መስፍን ብሩ የፌዴራል ፖሊሱን ተወዳደሪ ቢኒያም አበበን በነጥብ ማሸነፍ ችሏል።

በ75 ኪሎ ግራም የማራቶን ክለብ ተወዳዳሪው ተመስገን ምትኩ የአዲስ አበባ ፖሊሱን ተወዳዳሪ ማርሸት በራሶን በዝረራ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በ75 ኪሎ ግራም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተወዳዳሪ ባምላክ ደጉ የድሬዳዋ ከነማውን ተወዳዳሪ ማስረሻ ደጉን በበቃኝ አሸንፎታል።

በ81 ኪሎ ግራም የአዲስ አበባ ፖሊሱ ሰይፋ ከበደ የፌዴራል ፖሊሱን ተወዳዳሪ አብዱልፈታ ከማልን በዝረራ የረታው ሲሆን በተመሳሳይ 81 ኪሎ ግራም የማራቶን ክለብ ተወዳዳሪው ገዛሀኝ ሮባ የድሬዳዋ ከነማውን አላዩ አበበ በነጥብ አሸንፏል።

በ91 ኪሎ ግራም የፌዴራል ፖሊሱ ሙሉቀን መልኬ የአዲስ አበባ ፖሊሱን ታምራት አበበ በዝረራ ያሸነፈ ሲሆን በተመሳሳይ በ91 ኪሎ ግራም የድሬዳዋ ከነማው ሊበን አህመድ የደሴ ከነማውን ወንደሰን ይማምን በነጥብ ማሸነፍ ችሏል።

በሴቶች 54 ኪሎ ግራም የአዲስ አበባ ፖሊሷ ገነት ጸጋዬ የደሴ ከነማዋን ትዕግስት ገብረእየሱስን በበቃኝ ስታሸንፍ በተመሳሳይ 54 ኪሎ ግራም የድሬዳዋ ከነማዋ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ የኢትዮጵያ የወጣቶችና ስፖርት አካዳሚዋን ሀብታም ልዑልን በነጥብ አሸንፋለች።

በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር የዛሬ የሶስተኛ ቀን ውሎ ትናንት በሁለቱም ጾታዎች በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር በህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ እና ሁለተኛው ዙር በወላይታ ሶዶ ከተሞች መካሄዱ የሚታወስ ነው።

አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

 በደሴ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም