የኢትዮ-ኬንያ ሞያሌ አዋሳኝ ማህበረሰቦች የዘላቂ ሰላም ግንባታ የምክክር መድረክ ለዘላቂ ልማት መሰረት ጥሏል

50

ሚያዝያ10/2011በሞያሌ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን አስመልክቶ የተካሄደው የሰላም ጉባዔ ግጭቱን በመፍታትና የህዝቦቹን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትና ልማት የሚያረጋግጥ መሰረት የተጣለበት መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮኬንያ ሞያሌ አዋሳኝ ማህበረሰቦች የዘላቂ ሰላም ግንባታ የምክክር መድረክ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደሆነም ተገልጿል።

ትናንትናና ዛሬ የተካሄደው የምክክር መድረኩ መጠናቀቁን አስመልክተው የሁለቱ አገራት ተወካዮች መግለጫ ሰጥተዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዘይኑ ጀማል እንዳሉት የጉባዔው ዓላማ በሞያሌ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሳቦች ግጭትን በመፍታት በሰላምና በጋራ ተባብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠርን ያለመ ነው።

በቅርቡ በማህበረሰቦቹ መካከል የተፈጠረው ግጭት በድንበሩ አካባቢ አለመረጋጋትን ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በውይይቱም እነዚህን ግጭቶች በዘላቂነት በመፍታት በድንበሩ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ኑሯቸው እንዲሻሻል፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግና ልማት እንዲስፋፋ በሚያደርጉ ሁኔታዎች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ድህነትን ማስወገድ፣ የግጦሽና የውሃ ችግር በመፍታት በቀጣይ ሁለቱን ህዝቦች በጋራ ተግባብተው የሚኖሩበትን ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚሰራም ያመላከተ ነው ብለዋል።

አቶ ዘይኑ አክለውም ምክክሩ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኬንያ በኩል የተወከሉት አምባሳደር ቱኔያ ሁሴን ዳዶ በበኩላቸው በሁለቱ ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ የተነሱ ሐሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ የሁለቱ አገራት መንግስታት ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ለዚህም ለሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ህዝቦች በሰላም እንዲኖሩ ይሰራሉም ብለዋል።

ለዘላቂ የማህበረሰቡ ሰላማዊ ኑሮም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል አምባሳደሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም