ሸኮ የተፈጥሮ ደን ጉዳት ሳይደርስበት ተጠብቆ እንዲቆይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

332

ሚያዝያ 10/2011ሸኮ የተፈጥሮ ደን ጉዳት ሳይደርስበት ተጠብቆ እንዲቆይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና አርብቶ አደር ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው በቤንች ማጂ ዞን በሸኮ ወረዳ በሚገኘው የተፈጥሮ ደን ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሊሬ አቢዮ አካባቢው ሀገር በቀል እፅዋቶችንና ብዝሃ ህይወትን እንዳቀፈ በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

“በደኑ ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ከማህበረሰቡ ጋር በነበረን ውይይት ተገንዝበናል” ያሉት ሰብሳቢው የደን ሀብቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ተገቢ እንክብካቤ  ሊደረግለት እንደሚገባ ገልጸዋል።

“ነዋሪው ደኑን በማይጎዳ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ሊፈጠር ይገባልም” ብለዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባለ ወይዘሮ ወይንሸት መልኩ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብቱን ለመንከባከብና ለመጠበቅ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የቤንች ማጂ ዞን ደን አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ በበኩላቸው ለተፈጥሮ ደኑ ጥበቃ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በደን ሀብቱ ላይ ጉዳት ያደረሱ 12 ግለሰቦች ተይዘው ቅጣት እንደተላለፈባቸውም አስታውቀዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ ደኑን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት በደንና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው።

ህብረተሰቡ በባህላዊ የደን ልማትና አጠባበቅ ባህሉ  ደኑን ጠብቆ ማቆየቱን ያስታወሱት አቶ ውብሸት ይህ መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሸኮ ወረዳ 62 ከመቶ የሚሆነው በደን ሀብት የተሸፈነ መሆኑን ከወረዳው የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።