የመንግስት ፖሊሲዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ምሁራን በምርምርና ጥናት ማገዝ እንዳለባቸው ተጠቆመ

56

መቀሌ ሚያዝያ 10/2011 የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የላቀ ውጤት እንዲያመጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በምርምርና ጥናት ማገዝ እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ  ያዘጋጀው ዓመታዊ  የምርምር ኮንፈረንስ  በተቋሙ ዋና ግቢ ዛሬ ተጀምሯል።

ኮንፍረንሱ ሲጀመር የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንዳሉት፣መንግስት የሚያወጣቸው የተለያዩ የልማት ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች በምርምርና ጥናት ማስደገፍ ወሳኝ ነው።

"መንግስት እያካሄደ ያለውን የፀረ ድህነት ትግልና የድህነት መጠንን አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ለመቀነስ በጥናትና ምርምር ሲደገፍ የበለጠ መነቃቃትን ይፈጥራል"  ብለዋል።

በስራ እድል ፈጠራ፣በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት፣ በመሰረተ ልማት መስፋፋትና በቱሪዝም ዘርፍ እየታዩ ያሉትን ማነቆዎች በምርምር አስደግፈው መፍትሄ እንዲበጅላቸው ለፖሊሲ አውጪዎች ጥናትን መሰረት ያደረጉ ገንቢ ሃሳቦችን ምሁራን በማቅረብ እንዲያግዙ  ዶክተር አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

የከተሞች መስፋፋት ለኢንዱስትሪ ልማትና ለኢንቨስትመንት የሚኖራቸው ፋይዳ ዙሪያ ምሁራን ቢሳተፉ ሀገራቸውና ህዝባቸውን የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚያደርጉ ትኩረት እንዲሰጠውም አመልክተዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በበኩላቸው ፣ዩኒቨርስቲው የሚያካሂዳቸው የምርምር ስራዎች በዋነኛነት የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋሙ በሚያካሂዳቸው የምርምር ስራዎች   የመንግስትን አቅጣጫ መሰረት ያደረጉና ጥራት ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የዩኒቨርስቲው የምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ገብረህይወት ታደሰ  እስካለፈው ጥር ወር ድረስ ከ100 በላይ የምርምር ስራዎች እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከምርምር ስራዎች መካከልም በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የሚገኘውና በጣእሙና በይዘቱ የሚታወቀው የጉንዳጉንዶ ቡርቱካን ተመሳሳይ የአካባቢ ስነምህዳር ባላቸው የአፋርና የትግራይ ሌሎች አካባቢዎች የማላመድ ስራ  በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ሰላምና ደህንነት በአፍሪካ ቀንድ ስላለበት ሁኔታ በፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ጽሁፍ  ቀርቧል።

"በአፍሪካ ቀንድ እየታየ ያለውን ግጭት አሁን የመጣ ሳይሆን ለዘመናት የቆየና እስካሁን ሳይፈታ የቆየ ችግር ነው" ብለዋል።

በሃይማኖት፣ በዘር፣ በግጦሽና በድንበር ሰበብ የሚነሱ ግጭቶች ህዝቡን ወደ ባሰ ድህነት እንዲገባ ሲያደርጉት መቆየታቸው ፕሮፌሰር መድሃኔ አመልክተዋል።

ኢትዮጰያ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተሞች መስፋፋትና የፌዴራሊዝም ስርዓት መጠናከር ለልማት ስለሚኖራቸው ፋይዳና እያጋጠሙት ስላሉት ተግዳሮቶች በሌሎች ምሁራኖች ሃሳቦች ቀርበዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ኮንፈረንስ በዩኒቨርስቲው ከሚገኙ የተለያዩ ኮሌጆች የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው፤ የምርምር ውጤቶችችም ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም