የብርቅዬዎችን አምባ እንታደግ !

366

መሀመድ ረሻድ /ጎባ ኢዜአ/

የርቀት መለኪያዎችን ወደ ምንምነት እንድንቀይር የሚያደርግ ውብ ስፍራ! ከመዲናይቱ  አዲስ አበባ 411 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ሲደርሱበት የመጡበትን ድካም የሚያስረሳ የሚያሳሳ ውብ የተፈጥሮ ሃብት ውስጥ የሚያንሳፍፍ ከተፈጥሮ የሚያዛምድ የሚያዋድድ ድንቅ መስህብ ባለቤት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባሌ ዞን የሚገኘው ይህ ፓርክ በሃገራችን ውስጥ ከሚገኙ 27 ብሄራዊ ፓርኮችና ሌሎች ጥብቅ ስፍራዎች አንዱ ሲሆን በውስጡ በርካታ የብዝሃ-ህይወት ሃብትን አትረፍርፎ  የያዘና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ሥፍራ ነው። ወደ ፓርኩ ሲደርሱ ባሌ ዞን ዲንሾ ወረዳ ላይ የፓርኩን አስተዳደር ዋና ጽህፈት ቤት ያገኛሉ ።እንደምንም ይድረሱ እንጂ እንኳን መጣሁ እንዲሉ የሚያደርግዎት የተፈጥሮ ጸጋ በሰፊ እጁ ይቀበልዎታል።

በ1962 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ በ 2 ሺህ150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ተከልሎ የሚጠበቅ ይህ ብሔራዊ ፓርክ በፓርኩ ውስጥ ከ1 ሺህ600 በላይ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች፣ ከ78 ዓይነት በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት እና 300 የሚደርስ ዝርያ ያላቸው አዕዋፍ ይዟል። ከነዚህመካከል 32 የእጽዋትዝርያዎችእና 31 ብርቅዬ የዱር እንስሳት በብሔራዊ ፓርኩ ብቻ እንደሚገኙ ከብሔራዊ ፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የሳነቴአምባ የፓርኩን ለየት ያለ ስፍራነት የሚያረጋግጥ ልዩ መስህብ የሚታይበት ቦታ ነው።ስፍራው በአፍሪካ ካሉት ፕላቶዎች በስፋቱ 17 በመቶ የሚሸፍን ሜዳማና ትልቁ የአፍሮ አልፓይን አምባነው፡፡ይህ ውርጫማ ቦታ የከፍተኛ ተራራዎች መገኛ ሲሆን በሀገራችን በከፍታው ሁለተኛ የሆነው እና ከባህር ጠለል በላይ 4ሺህ 377 ሜትር ከፍታ ያለው የቱሉ ዲምቱ ተራራም በዚሁ ስፍራ ይገኛል፡፡

የሳነቴ አምባ ከመልከአ ምድሩ አቀማመጥ ባሻገር የዝናብ ውኃን የመሰብሰብና የማጣራት አቅም ያለው የኬኒያ ና የሶማሊያን ህዝቦችን ጨምሮ ከ12 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ህልውና የሆኑ ከ40 በላይ ተፋሰሶች የሚፈለቁበት የዋቤ ሸበሌ፣ ገናሌ ዋቤ እና የመሳሰሉት ትላልቅ ወንዞች መነሻ ቦታ ነው፡፡ 

ሌላው የፓርኩ አካል በሀገራችን በጥቅጥቅ ደን ሽፋኑ ከያዮ ደን ቀጥሎ የሁለተኛነትን ስፍራ የያዘው የሀረና ደንም መገኛው እዚሁ ፓርክ ውስጥ ነው፡፡የተፈጥሮ ደኑ የፓርኩን አንድ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሸፍናል፡፡ ደኑ ከሀገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ተረጋግጦ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት በሚያስችለው ፕሮግራም ውስጥ ለካርቦን ንግድ ከታጩ የሀገራችን ድንቅ ደኖች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

በውስጡ ባሉት የእጽዋት እና የእንስሳት ብዝሃ ህይወት ሲታዩ ከዓለም በ34ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ በ12ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በዘርፉ የተፃፉ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ፓርኩ በውስጡ አቅፎ ከሚገኘው እጽዋትና እንስሳት ብዝሃ ህይወት በተጓዳኝ ለአዕዋፍ ዝርያ ካለው ምቹ ሁኔታ የተነሳ “በርድ ሳይት ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ዓለም አቀፍ  ድርጅት ‹‹በዓለም ከሚገኙ ምቹ የአዕዋፍ መገኛ አንዱ›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ከላይ የጠቃቀስናቸውን እውናታዎችና ሌሎችን የፓርኩን እምቅ አቅም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እ.አ.አ. በ2009 በጊዜያዊ መዝገቡ ላይ አስፍሮታል። ይህ በብዝሐ ህይወት ስብጥሩና የተንበሸበሸው የብርቅዬዎች አምባ በአሁኑ ወቅት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ስጋት ተጋርጦበታል፡፡ ፓርኩንና  በውስጡ  የሚገኘውን ብዝሃ ህይወት እየተፈታተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች መካከል ሰደድ እሳት፣ ህገወጥ ሰፈራ፣የእርሻ መሬት ማስፋፋትና ልቅ ግጦሽ በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አስቻለው ጋሻው ይናገራሉ፡፡

በተለይም በፓርኩ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘው ሰደድ እሳት ብርቅዬ የዱር እንስሳት መኖሪያቸውንና ምግብቸውን እያሳጣቸው ይገኛል።እንዲሁም መብረርና መራመድ የማይችሉ ብዝሓ ህይወት ዝርያዎች መጥፋት፣በአይን የማይታዩና ደቂቅ አካላት መውደምና ሌሎች ተጽዕኖዎችከባድ እየሆኑመጥተዋል።

የዚህ ፓርክ የሰደድ እሳት በተለይ በባሌ ህዝብ ዘንድ ጠባሳን ጥሎ ማለፉን ነው አቶ አስቻለው የሚያስታውሱት፡፡ በ2007 ዓ.ም በዚሁ ፓርክ ላይ በህገ ወጥ ሰዎች የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ጥረት ሲያደርግ ህይወቱን በእሳት ያጣውን የፓርኩሰራተኛና የአካባቢ ተቆርቋሪ የነበረው ወጣት ቢኒያም አድማሱን በማሳያነት አቅርቧል፡፡ ለዚህ ወጣት የተፈጥሮ ሀብት ጀግና በሚል በፓርኩ ውስጥ ሀውልት የቆመለት ቢሆንም ጠባሳው በብዙ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ነው፡፡የእሳት አደጋው ዛሬ ምድረስ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ደግሞ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው፡፡

ዘንድሮም በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በብሔራዊ ፓርኩ ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ 300 ሄክታር በሚበልጥ አስታ በመባል በሚታወቅ እጽዋት ላይ ጉዳት  መድረሱን ነው የተነገረው፡፡ በፓርኩ ላይ ተከስቶ የነበረውን የሰደድ እሳት በባህላዊ መልኩ ለማጥፋት በተደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች አስተዋጽኦ አቅምበፈቀደ መጠን ያደረጉት ርብርብ ጊዜያዊ መፍትሔ አስገኝቷል። በተለይ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  ያደረጉት ተሳትፎ ዛሬም የሀገሪቱን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፍ ወጣቶች ዘንድ ላለው ቁርጠኛነት ጉልህ ማሳያ ሆኗል።

በቀጣይ በተፈጥሮ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ ሲከሰት በባህላዊ መልኩ ለማጥፋት ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ አደጋውን አስቀድሞ በመከላከልና  ሲከሰትም ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት በእንስሳት እና  እጽዋት ህይወት ላይ  ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት በቃጠሎው ወቅት በእሳት ማጥፋቱ ሂደት የተሳተፉት አቶ ሀሰን በከር ናቸው።

በተለይ ባሌን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ፓርኮች ላይ የተጋረጠውንሰውሰራሽተግዳሮት መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት ካልተቻለ የብዝሓ ህይወት ሀብቱ አደጋ ላይ የመውደቁ ጉዳይ እንደማያጠራጥር ይናገራሉ።አቶ ሀሰን እንዳሉት በፓርኩ አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፓርኩ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ይሄ ደግሞ የባለቤትነት ስሜት በሚፈለገው ደረጃ እንዳያዳብሩ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመቀነስ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከብሔራዊ ፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮች ተጠቃሚ በማድረግ የባለቤትነት መንፈሱን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ።

ብሔራዊ ፓርኩን የሚያዋስኑ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለብዝሐ ህይወትጥቅምና ተጓዳኝ  ጉዳዮች ላይ ተከታታይነት  ያለው የግንዛቤ ማጎልበቻ ስራ ከመስራት በተጓዳኝ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰዱ የህግ እርምጃዎች አስተማሪ መሆን እንዳለባቸው የተናገረው ደግሞ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ የትምህርት ክፍል ተማሪ ኤቢሳ ቶላ ነው፡፡

ፓርኩን በሚያዋስኑ ወረዳዎች ላይ እየሰሩ ከሚገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ የፍራንክፈርት ዞሎጂካል ሶሳይት አንዱነው፡፡ የፕሮጀክቱ የባሌ ዞን አስተባባሪ አቶሁሴን ኢንድሪስ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በፓርኩ አካባቢ በሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ናቸው፡፡

በተለይ ማህበረሰቡ ከፓርኩ ወሰን ውጪ በሌሎች የስራ መስኮች በመሰማራት ህይወቱን እንዲለውጥ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተከናወኑ በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ይሄ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት ፓርኩን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ የሚያደርገውን ጥረት በቀጣይነትም እንደሚቀጥልበት ተናግረዋል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ ፓርኮች ላይ ከሰው ጋር  ባላቸው ግንኙነት  ምክንያቶች የሚከሰቱትን አደጋዎችና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን በወቅቱ የገለጹት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞንመኮንን ናቸው።

በመሆኑም ባለሥልጣኑ በሁሉም ቦታዎች በአንድ ጊዜ መተግበር ባይችልም የእሳት አደጋ በሚያሰጋቸው አካባቢዎች የእሳት አደጋ መከላከያ ግብረ-ሀይል ለማቋቋም በትኩረት እየሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በእሳት ቅድመ-መከላከል ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ተከታታይነት  ያለው ትምህርት መስጠትና በአጥፊዎች ላይ በሚወሰደው የእርምት እርምጃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጂት መስራት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።

አሁን እየደረሰበት ያለውን ሰው ሰራሽ ጉዳት በመቀነስም ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት በዩኔስኮ በቋሚ መዝገብ ውስጥ ለማስፈር ሁሉን አቀፍ ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

እንደዚህ ያሉ አስገራሚ የተፈጥሮ ሃብት ያለባቸውን ብሔራዊ ፓርኮች መንከባከብና ለቱሪዝም ልማት መጠቀም ሃገሪቱ ከዘርፉ ልገኝ የምትችለውን ጥቅም የሚያጎለብት እንደመሆኑ ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ መስራት ይጠበቅበታል። ዘመናትን የተሻገረውን ውብ የተፈጥሩ በአግባቡ ተንከባክቦ በቀላሉ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል እንደዋዛ በሚከሰቱ ጥፋቶች ለውድመት ማጋለጥ የህሊናም የትውልድም ተወቃሽ የሚያደርግ ነውና ሁሉም ተገቢውን ጥበቃ በማድረጉ በኩል የድርሻውን ይወጣ መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም