የግሉን ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ስርአት መፍጠር ያስፈልጋል ተባለ

84

አዲስ አበባ ሚያዝያ 10/2011 የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግሉን ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ መልካም የኩባንያ አስተዳደር ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል አለ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግሉ ዘርፉ በሀገሪቱ ጥቅል ምርትና ኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ቢችልም ሥነ ምግባራዊ የንግድ አሰራር ጉድለት ይስተዋልበታል።

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ለኢዜአ እንደገለጹት ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ አሰራር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘላቂነት ላይ ጥላ አጥሎበታል።

በኢትዮጵያ የግል ኩባንያዎች ትክክለኛ የውድድር መንፈስ እየጠፋ፤ በምትኩ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት ተንሰራፍቷል ብለዋል።

ይህ ደግሞ የግሉን ዘርፍ ጤናማ ውድድር በማበላሸት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሚዛን በማሳት በጥርጣሬ የተሞላ የንግድ ስርዓት፤ በዜጎች ላይ የከፋ የኑሮ ውድነት እንዲመጣ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በስሩ የኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ሚዛናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፉ ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን በተቋማት የሚተገብሩ የመልካም ኩባንያ አስተዳደር ደንብ አውጥቷልም ነው ያሉት።

በሁሉም የንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢዎች ፍትሃዊ የንግድ አሰራር እንዲሰርፅ እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችል ደንብ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመሆኑም የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች በንግድ ውድድሩ ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም