ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ።

157

ሚያዝያ 10/2011የ19 አመቷ ታዳጊ ሰሚራ ሙሳ ከ10 አመት በፊት በማዕከሉ የልብ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት የልጅነት ጊዜዋን ከጓደኞቿ ጋር ቦርቃ ተምራ ዛሬ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት።

ሰሚራ ከ10 ዓመት በፊት ሲያስጨንቃት የነበረው የልብ ህመም ዛሬም በድጋሚ ከትምህርት ቤት እንድትቀር አድርጓታል፣ በማዕከሉ በምታደርገው ክትትል ድጋሚ ቀዶ ጥገና ሊደረግላት ወረፋ እየጠበቀች ትገኛች።

በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ልክ እንደ ሰሚራ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ለማግኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ሜዲካል ዳሬክተር ዶክተር ሄለን በፈቃዱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ማዕከሉን ባጋጠመው የህክምና ቁሳቁስ እጥረትና የራሱ በጀት አለመኖር በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ አድርጎታል።

በማዕከሉ ያሉት ባለሙያዎች አገልግሎቱን ሳምንቱን ሙሉ የመስጠት አቅም ቢኖራቸውም ባለው ችግር ምክንያት አሁን የሚሰጡት አገልግሎት በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።

"ይህንን ኽርት ቲም እንዲሰራ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱን እንዲሰጥ የሁላችንም ሃላፊነት ነው" ሲሉ ዕከሉ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ የሁሉንም እገዛ ጠይቀዋል።

ማዕከሉ በዘላቂነት እራሱን ችሎ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ህብረተሰቡ ድጋፍ የሚያደርግባቸው መንገዶች እንደሚዘረጉ ተናግረው በዚህም ማንኛውም ሰው የቻለውን ድጋፍ እንድያደርግ ጠይቀዋል።

በማዕከሉ ጉብኝት ያደረጉት አምባሳደር ሱለይማን ደንዴፎ አሁን ያጋጠመው እጥረት "አርቴፊሻል እጥረት ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለህዝብ የሚያስተዋውቅበትንና ድጋፍ የሚያገኝበትን አሰራር ቢዘረጋ ከአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መድረስ ይችላሉ ብለዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያን ወክለው በሚሄዱበት አገር ማዕከሉ እገዛ እንዲያገኝ ተልዕኮ እንደሚወስዱ ገልጸው በዘላቂነት እራሱን እንዲችል አለም አቀፍና አገር አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ስራውን እንዲያጠናክር መክረዋል።

የማዕከሉ የበላይ ጠባቂ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው በቋሚነት በየትኛውም የአለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ዘመናዊ የገቢ ማሰባሰቢያ አሰራር በመዘርጋት ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

በቀጣይም ማዕከሉ በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራትን እቅድ በማውጣት መስራት እንደሚገባ በመምከር የቻሉትን እገዛ ለማድርግ ቃል ገብተዋል።

ከኢትዮጵያውያም ባለፈ የአፍሪካ የልብ ህክምና ማዕከል እንዲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያን እገዛ እንዲያደርጉ መረጃ ለመስጠትም እንዲሁ።

ማዕከሉ ባለፉት 10 ዓመታት ለ4 ሺህ 800 የልብ ህሙማን የቀዶ ጥገና ህክምና መስጠቱን ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም